በሶማሌ ክልል የተጀመሩ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች የዜጎችን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል የተጀመሩ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች የዜጎችን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡ ነው
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 9/2016 (ኢዜአ)- በሶማሌ ክልል የተጀመሩ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች የዜጎችን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡና ከተሞችንም እያዘመኑ መሆኑን የቀብሪ ደሀር እና ደገሀቡር ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።
በሶማሌ ክልል የሚከበረውን የብሄር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዝግጅት ለመዘገብ ጅግጅጋ የሚገኙ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በክልሉ ያሉ የልማት ስራዎችን እየጎበኙ ነው።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎቹ በቀብሪ ደሀር እና ደጋ ሀቡር ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ከጎበኟቸው መካከል ይጠቀሳሉ።
በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በመንገድ ግንባታ፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በውሃ ልማትና በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ምልከታ አድርገዋል።
የቀብሪ ደሀር ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር አብዲረዛቅ አወል፤ ከለውጡ በኋላ በሁሉም ዘርፍ ሰፋፊ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው በተለይም የመንገድ፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ የውሃና የመብራት ኃይል የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
የደገሀቡር ከተማ ከንቲባ በሽር ዬሱፍ፤ በከተማዋ መንገድን ጨምሮ ሌሎችም የመሰረተ ልማት ስራዎች በስፋትና በጥራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
የከተማዋን የንግድና ኢንሸቨስትመንት አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል ባለሃብቶች በተለያዩ የልማት መስኮች እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የቀብሪ ደሀር ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብዱሂላል አብዱላሂ እና የደጋሀቡር ከተማ የብልጽግና ፓርቲ አባል መሀመድ ሱሀል፤ የቀብሪደሀር እና ደጋሀቡር ከተሞች ከየትኛውም አካባቢ የመጡ ዜጎችን በፍቅርና አብሮነት የሚሰሩባቸውና የሚኖሩባቸው ውብ ከተሞች መሆናቸውን ጠቅሰው ባለሃብቶች መጥተው ኢንቨስት እንዲያደረጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የቀብሪ ደሀር ከተማ ሥራ አስኪያጅ አሊ መሀመድ፤ የመሰረተ ልማት አውታሮች የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እያሻሻሉ መሆኑን ጠቅሰው ባለሃብቶችን በልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።
በቀብሪ ደሀር ከተማ የሚኖረው ወጣት አብዲ አባስ፤ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ እየተሰሩ ያሉ የልማት ሥራዎች የሚበረታቱ መሆኑን ገልጿል።
በደጋሀቡር ከተማ የመንገድ ግንባታ እያከናወነ የሚገኘው የተወከል ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ፕሮጀክት መሀንዲስ እዮብ ሽታዬ፤ የመንገድ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜና በጀት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግሯል።
የሶማሌ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፈርሃን ጅብሪል፤ በለውጡ ዓመታት የክልሉን ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ ዐበይት የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ ከ2 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ መገንባትና ከ66 በላይ ከተሞችን የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የተደረገበትን ስራ ለአብነት ጠቅሰዋል።
በፌደሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ህዳር-25 የወንድማማችነት፣ ህዳር-26 የብዝሃነት፣ ህዳር-27 የአብሮነት፣ ህዳር-28 የመደመር፣ ህዳር-29 የኢትዮጵያ ቀን በሚሉ ስያሜዎች በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ይሆናል።
በጅግጅጋ ከተማ በሚኖረው ዝግጅትም የባህላዊ አልባሳት ትዕይንት፣ ስፖርታዊ ውድድር፣ የንግድ ትርዒትና ባዛር፣ የምክክር መድረክና ሲፖዚየም ይኖራል።