በእጃችን ያለውን እምቅ ሀብት በመጠቀም የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ተዘጋጅተናል- የመንግስት አመራር አባላት - ኢዜአ አማርኛ
በእጃችን ያለውን እምቅ ሀብት በመጠቀም የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ተዘጋጅተናል- የመንግስት አመራር አባላት

ጂንካ ፤ህዳር 9/2016 (ኢዜአ)- በእጃችን ያለውን ዕምቅ ሀብትና አቅም በመጠቀም የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሰሩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጂንካ ማዕከል ስልጠና እየወሰዱ ያሉ የመንግስት አመራር አባላት አስታወቁ።
''ከዕዳ ወደ ምንዳ'' በሚል መሪ ሀሳብ ከአገሪቱ አራቱም አቅጣጫዎች ተውጣጥተው በጂንካ ማዕከል ስልጠና እየወሰዱ ያሉ የመንግስት አመራሮች በጂንካና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
ከጥቅምት 30 እስከ ህዳር 12 በሚቆየው ስልጠና በጂንካ ማዕከል 700 የሚሆኑ አመራሮች ስልጠናውን እየተካፈሉ ይገኛሉ።
በዛሬው ዕለት ደግሞ አመራሮቹ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለማሻሻል የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ጎብኝተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው ከሚገኘው የእንስሳት ሀብት የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ዘመናዊ በሆነ መልኩ የተሻሻሉ የወተት ላሞች፣ የተሻለ ዝርያ ያላቸውን እንቁላል ጣይ ዶሮዎችና የተሻሻሉ ፍየሎችን የማላመድ ስራ እየሰራ ይገኛል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ ለጉብኝዎቹ ባደረጉት ገለፃ ዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል አድርጎ ከሚሰራቸው የትኩረት መስኮች አንዱ ግብርና መሆኑን ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ ጥቂት አመታት ቢሆኑትም በአካባቢው ካለው የእንስሳት ሀብት የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ላይ አተኩሮ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ላይ የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ውጤት እየተገኘባቸው መሆኑን ጠቅሰው ከእንስሳት እርባታው የሚገኘውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ እያቀረበ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተለይ በዩኒቨርሲቲው የዝርያ ማሻሻል የሚሰራባቸው የወተት ላሞች፣ ከአካባቢው ላሞች ጋር ሲነፃፀሩ በእጥፍ ምርት የሚሰጡ በመሆናቸው የአርሶና አርብቶ አደሩን ህይወት ከመለወጥ አኳያ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
ለአብነትም ከአካባቢው ላሞች በቀን ግፋ ቢል እስከ ሁለት ሊትር ወተት የሚገኝ መሆኑን አንስተው በዩኒቨርሲቲው የዝርያ ማሻሻል ስራ የሚሰራባቸው ላሞች በቀን ከ20 ሊትር በላይ ወተት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በተጨማሪም በእንቁላል ጣይ ዶሮዎች እና በፍየሎች ላይ የዝርያ ማሻሻል ሥራ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
በቀጣይም በዩኒቨርሲቲው በእንስሳት ማላመድ ስራው የተገኘውን ውጤት ለአርሶና አርብቶ አደሮች እንደሚያሰራጭ ተናግረዋል።
ሰልጣኝ አመራሮች እንዳሉት በጉብኝቱ ጥሩ ዕውቀትና ልምድ እንዳገኙ ገልፀው ያገኙትን ልምድ ወደ አካባቢያቸው በመውሰድ አርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የማረቆ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪ አቶ ከድር ሙሐመድ በጉብኝቱ ጥሩ ልምድና ዕውቀት ማግኘታቸውን ገልፀው ከስልጠናው የትኩረት መስኮች አንዱ በአካባቢ የሚገኘውን ዕምቅ ሀብት በመለየትና በማልማት የህዝቡን የልማት ጥያቄ መመለስ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከስልጠናውና በጉብኝቱ ያዩትን ልምድና ተሞክሮ በአካባቢያቸው ተግባራዊ በማድረግ የልዩ ወረዳውን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ከሲዳማ ክልል የሁላ ወረዳ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሰማ ለገሰ በበኩላቸው ከዕዳ ወደ ምንዳ በሚል መሪ ሀሳብ እየተሰጠ ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠና ብዙ ዕወቀት ያገኘሁበት ነው ብለዋል።
ይህን ያገኘሁትን ጠቃሚ ዕውቀት ወደ አካባቢዬ ስመለስ ወደ ተግባር በመቀየር የህዝቡን የልማትና የመልካም አሰተዳደር ጥያቄ ለመመለስ ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።
ከወላይታ ዞን ቦሎ ሶምቦቤ ወረዳ ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አልማዝ ሀይለሚካኤል በበኩላቸው ከዕዳ ወደ ምንዳ በሚል መሪ ሀሳብ እየተሰጠ ያለው ስልጠና አገራዊ፣ አህጉራዊና አለም አቀፍዊ ዕውቀቶችን ያገኘንበት፣ የሀገራችንንም ነባራዊ ሁኔታ በጥልቀት ያየንበት ነው ብለዋል።
“በተለይ በአካባቢያችን እምቅ ሀብቶች ቢኖሩም ሀብቶቹን ለይቶ ጥቅም ላይ ከማዋል አኳያ ክፍተቶች የነበሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከስልጠናው ሀብቶቹን በመለየት እንዴት ኢኮኖሚያዊ ሀብት ማመንጨት እንደምንችል የሚያስገነዝብ ዕውቀት አግኝቻለሁ” ብለዋል።
ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው ልምድና ተሞክሮ በግብርናው መስክ የሚሰሩ የልማት ስራዎችን ለማሳካት አቅም እንደሚፈጥር ገልፀው በቀጣይም ያገኙትን ልምድ በእንስሳት እርባታው የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
ጉብኝቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማዕከል ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተመስገን ቡርቃና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መሪነት እየተካሄደ ነው።