ጅግጅጋ ከተማን ማራኪ የንግድና ኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጅግጅጋ ከተማን ማራኪ የንግድና ኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 9/2016 (ኢዜአ) ፦ ጅግጅጋ ከተማን የምስራቅ ኢትዮጵያ ማራኪ የንግድና ኢንቨስትመንት የስበት ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ ኢንጂነር ዚያድ አብዲ አህመድ ገለጹ።
የሶማሌ ክልል 18ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ለማስተናገድ የዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁንም አስታውቋል።
የበዓል ዝግጅቱን ለመዘገብ ጅግጅጋ የሚገኙ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በክልሉ ያሉ የልማት ስራዎችን እየጎበኙ ነው።
በጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በመንገድ ግንባታ፣ በስታዲየም፣ በአረንጓዴ ስፍራ የወጣቶች መዝናኛ፣ በውሃ ልማትና ሌሎችም ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎችን ጎብኝተዋል።
ከጉብኝቱ በኋላ ማብራሪያ የሰጡት የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ዚያድ አብዲ አህመድ፤ ጅግጅጋ ከተማ የአብሮነት፣ የሰላም፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ስትራቴጂክ ምቹነት ያላት ከተማ ናት ብለዋል።
በከተማዋም 40 ኪሎ ሜትር የአስፓልት የመንገድ ግንባታ፣ ከ30 በላይ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና ሌሎችም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በከተማዋ ከፍተኛ የንግድና ኢንቨስትመንት መነቃቃት እያሳየች መሆኗን ተናግረዋል።
እንደ አጠቃላይ ጅግጅጋ ከተማን የምስራቅ ኢትዮጵያ ማራኪ የንግድና ኢንቨስትመንት የስበት ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ለ18ኛው የብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች በዓል አከባበር አስፈላጊ የሆኑ የዝግጅት ሥራዎች የተጠናቀቁ መሆኑንም ከንቲባው ጠቁመዋል።
በፌደሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል "ብዝኅነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በጅግጅጋ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት እንደሚከበር የተያዘው መርኅ-ግብር ያመላክታል።