በታላቁ ሩጫ ውድድር በወንዶች ብንያም መሐሪ በሴቶች ደግሞ መልክናት ውዱ አሸነፉ - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ ሩጫ ውድድር በወንዶች ብንያም መሐሪ በሴቶች ደግሞ መልክናት ውዱ አሸነፉ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 9/2016 (ኢዜአ) ፦ በ23ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በወንዶች ብንያም መሐሪ በሴቶች ደግሞ መልክናት ውዱ አሸነፉ።
በአዲስ አበባ የተካሄደውና ከ45ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉበት የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተጠናቋል።
የዘንድሮው ውድድር "ለሁሉም ህፃናት ክትባት" በሚል መሪ ሀሳብ መነሻውንና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ ተካሂዷል።
በማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የሴቶችና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በባርሴሎና ኦሊምፒክ አትሌት ደራርቱ ቱሉን በመከተል በ10 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ያገኘችው ደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት ኤላና ሜር እና ታዋቂው እንግሊዛዊ ኮሜንታተር/የዘርፉ ተንታኝ/ ቲም ሃቺንግስ በክብር እንግድነት ታድመዋል።
በውድድሩ በወንዶች ብንያም መሐሪ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 1ኛ በመውጣት ሲያሸንፍ፣ ዘነበ አየለ በግል 2ኛ እንዲሁም ጂራታ ሌሊሳ 3ኛ በመውጣት አጠናቀዋል።
በሴቶች አትሌት መልክናት ውዱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንደኝነት፣ መገርቱ አለሙ ከኤሊት ስፖርት ማኔጅመንት ሁለተኛ እንዲሁም ተኪና አማረ ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል።
በሁለቱም ጾታዎች የውድድሩ አሸናፊ ለሆኑት አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ200 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓለም ከሚከናወኑ 10 ታላላቅ የጎዳና ላይ ውድድሮች መካከል አንዱ ሲሆን ከአፍሪካ በአንደኝነት ይጠቀሳል።
በ1994 ዓ.ም የተጀመረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከስፖርታዊ ውድድርነቱ ባሻገር የቱሪዝም መስህብ በመሆን ጭምር ኢትዮጵያን እያስተዋወቀ መሆኑም ይታወቃል።