ቀጥታ፡

በምርምር ተቋማት የተገኘውን የቡና ምርታማነት በአርሶ አደር ማሳ የማስፋት ስራ እየተከናወነ ነው 

ዲላ ፤ ህዳር 8/2016 (ኢዜአ)፡ - በምርምር ተቋማት የተገኘውን የቡና ምርታማነት በአርሶ አደር ማሳ ላይ የማስፋፋት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ። 

በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ ቡናን በቴክኖሎጂ አስደግፎ የማስፋት ስራዎች የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ እንዳሉት የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ከአርሶ አደሩና ከግብርና ሴክተሩ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።


 

"እንደ ሀገር በሄክታር የሚገኘውን 7 ኩንታል የቡና ምርት በእጥፍ ለማሳደግ የተሻሻሉ ዝሪያዎችን የመለየትና የማስራጨት ተግባራት እየተከናወኑ ነው" ብለዋል።

ለዚህም በምርምር ተቋማት በሄክታር 26 ኩንታል ምርት እንደሚሰጡ የተረጋገጠ ከ20 በላይ የተሻሻሉና የተዳቀሉ ዝሪያዎችን ቡና አብቃይ ለሆኑ አካባቢዎች ማሰራጨት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ከዝርያዎቹም በአርሶ አደር ማሳ ላይ 19 ኩንታል የቡና ምርት መገኘቱን በመስክ ምልከታው ወቅት ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል።

"የቡና ቴክኖሎጂ ዝርያ ከማሻሻል ባለፈ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅትና የአፈር ለምነት ጥበቃን እንደሚያካትትና በጉብኝቱም ይህንኑ ተመልክተናል" ብለዋል።

በምርምር ተቋማት የተገኝውን የቡና ምርታማነት በአርሶ አደር ማሳ በማስፋትና በኩታ ገጠም በማልማት ሀገራዊ የቡና ምርት አቅርቦትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ያረጁ ቡናዎችን በተሻሻሉ ዝሪያዎች በመተካት በሄክታር 6 ኩንታል ብቻ ይመረት የነበረውን የወረዳውን የቡና ምርታማነት በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ 19 ኩንታል ማድረስ እንደተቻለ ያነሱት ደግሞ የዲላ ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታሪኩ ታደሰ ናቸው።


 

በወረዳው ከወንዶ ገነትና አዋዳ የግብርና ምርምር ማዕከላት ጋር በመቀናጀት በ37 ክላስተሮች ከ48 ሄክታር በላይ ቡና በተሻሻሉ ዝሪያዎች እየለማ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ይህንንም የማስፋቱ ስራ በሁሉም የወረዳው ቀበሌዎች እየተከናወነ ነው" ብለዋል።

በመስክ ምልከታው ላይ የተገኙ የምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግሩም ጂብቾ በበኩላቸው በወረዳው ከ13 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና የተሸፈነ ቢሆንም በእርጅና ምክንያት የምርታማነት ችግር እንዳለበት ጠቅሰዋል።

ካለፈው አመት ጀምሮ ከምርምር ተቋማት ጋር በመቀናጀት በ7 ቀበሌዎች 4 ሺህ ሄክታር ያረጀ ቡና ነቅሎ በተሻሻሉ ዝሪያዎች ለመተካት የማደስ ስራዎች መጀመራቸውን አስረድተዋል።

በመስክ ምልከታው የኩታ ገጠም የቡና ልማት የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ መረዳታቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ይህንኑ ለማስፋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለሰልጣን የቡናና ፍራፍሬ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ምንዳዬ ምትኩ፣ ከምርምር የተነጠለ የቡና ልማት ስራ ውጤቱ አነስተኛ ነው ብለዋል።

በክልሉ ከ165 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና እንደለማና 24 በመቶው ያረጀ በመሆኑ ምርታማነት ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል።

ያረጁ ቡናዎችን ከማደስ ባለፈ ከ36 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የቡና ቴክኖሎጂ መንደር መመስረት መቻሉን አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም