ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር የተሳካ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና እንወጣለን  - የዳያስፖራ አባላት  

አዲስ አበባ፤ህዳር 8/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር የጋራ መግባባት በማምጣት አገራዊ አንድነት እንዲጸና ለማስቻል የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የዳያስፖራ አባላት ተናገሩ። 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን "የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሚናና ተሳትፎ ለአገራዊ ምክክርና ለአገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ኃሳብ ከዳያስፖራ አባላት ጋር ተወያይቷል።   

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የዳያስፖራ አባላት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር የጋራ መግባባት ለመፍጠርና አገራዊ አንድነት ለማጠናከር ወሳኝ እርምጃ ነው።

በመሆኑም በዚህ በአገራዊ ምክክሩ በንቃት በመሳተፍና ለስኬቱም አስፈላጊውን ኃሳብ በማቅረብ አገራዊ አንድነት እንዲጠናከር የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል። 

ያሉንን ልዩነቶች ወደ ጎን በመተው ከግጭት ይልቅ በሰላም ችግሮችን ለመፍታት አገራዊ ምክክሩ ለውይይት እያመቻቸ ያለው ጉዳይ የሚበረታታ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሰላም ከሌለ በአገር ውስጥ ሰርቶ መኖርም ሆነ ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወን ስለማይቻል ለዘላቂ ሰላም በር የሚከፍተው አገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን አበክረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። 


 

ዳያስፖራው የአገራዊ ምክክሩ ሥራ እንዲሳካ ተሳትፎውን እንደሚያጠናክር የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማኅበር የቦርድ አባል ካፒቴን ሰለሞን ግዛው ናቸው።

የአገሪቱ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ዳያስፖራው እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የበኩሉን ሚና ይወጣል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር ሰብሳቢ ቅድስት ሉልሰገድ በበኩላቸው፤ በየትኛውም አገራት ያሉ ዳያስፖራዎች በአገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉና ውይይቱ የተሳካ እንዲሆን የበኩላችንን አስተዋጽዖ ማድረግ አለብን ብለዋል።  

 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ ጊዜ፤ ኮሚሽኑ  የተለያዩ የቅድመ ዝግጅትና የተሳታፊዎች ልየታ ጨምሮ ሌሎች ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልፀዋል።

አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የዳያስፖራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዳያስፖራው በምክክሩ ተሳትፎውን ማጠናከር አለበት ብለዋል።

እንዲሁም በምክክሩ ሂደት ዳያስፖራው ባለው እውቀት የኮሚሽኑን ሥራ ሊደግፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።

አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካና የኃሳብ መሪዎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የኃሳብ ልዩነትና አለመግባባት ላይ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር እየሰራ ነው።

አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን ማካሄድ የተሻለ አገራዊ መግባባትን ለመገንባት በሂደትም የመተማመንና ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ለማጎልበት መቋቋሙ ይታወቃል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም