ቀጥታ፡

ኪነ-ጥበብ ለአገር ሰላምና አንድነት መጠናከር የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ውጤታማ እንዲሆን ኢዜአ የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ህዳር 8/2016 (ኢዜአ)፡-ኪነ-ጥበብ ለአገር ሰላምና አንድነት መጠናከር የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ውጤታማ እንዲሆን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት/ኢዜአ/ የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግና ከኪነ- ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ገለጸ።

የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን የለውጥ ሥራዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በጋራ መሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ዜናና ዜና ነክ መረጃዎች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር አገራዊ ፋይዳቸው ከፍ ያሉ የፓናል ውይይቶችና ምክክሮችን እያዘጋጀ ይገኛል።    

ኪነ-ጥበብ ለአገር ዕድገት ማኅበረሰባዊ ለውጥና አካታች ሥርዓት ግንባታ ሚናው የጎላ  መሆኑን ጠቁመው፤ ዘርፉ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ ኢዜአ የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።    

ኪነ-ጥበብ ለሰላም፣ ፍቅርና አንድነት መጎልበት ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ በመሆኑ ኢዜአ መሰል አገራዊ ግብና ውጥኖች እንዲሳኩ ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

ኪነ-ጥበብ አገር በቀል እውቀቶች፣ የተደበቁ ማንነቶች እንዲሁም እውነታዎች የሚወጡበት ትልቅ መሳሪያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ በበኩሉ፤ ኪነ-ጥበብ ለማኅበረሰብ ለውጥና አገራዊ እድገት ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ ቢሆንም በተፈለገው ደረጃ ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን ጠቅሷል።    

ከዚህ አኳያ እንደ ኢዜአ ያሉ ተቋማት አብረው ለመሥራት መነሳሳታቸው የሚበረታታ ነው ብሏል።   

የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማኅበርም ከበርካታ መገናኛ ብዙኃን ጋር በትብብር መሥራት የሚያስችለውን ስምምነት እያደረገ መሆኑን ተናግሯል።    

ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በጋራ ለመሥራትና አገራዊ ግቦችን ለማሳካት ማኅበሩ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።   

 ኪነ-ጥበብና መገናኛ ብዙኃን የሚነጣጠሉ አይደሉም፤ በተለይም ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የሁለቱ አካላት ጥምረት ወሳኝ ነው ያለው ደግሞ ተዋናይና ገጣሚ ዋስይሁን በላይ ነው።

ኪነ-ጥበብና ሚዲያ ከተደጋገፉ የሕዝብን አንድነት ማጠናከርና ሰላምን ማጽናት ይቻላል ብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም