ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎችን ለማዘመን እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ህዳር 8/2016 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አዳዲስ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎችን በማዘመን ለኢትዮጵያ የሚመጥን የመረጃ ተቋም ለመሆን እየሰራ መሆኑን ገለጸ።   

የአፍሪካ ስታትስቲክስ ቀን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ተከብሯል።

ዕለቱ "የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ትግበራን ለማፋጠን የመረጃ ሥነ-ምህዳሮችን ማዘመንና የስታቲስቲክስ መረጃ በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ለውጥና ዘላቂ ልማት ውስጥ ያለው ሚና" በሚል መሪ ኃሳብ  ነው የተካሄደው።   

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ አህጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጠና እውን እንዲሆን ከፈረሙ አገራት የመጀመሪያዋ ናት።  

ትግበራውንም ለማፋጠን በባለቤትነት የያዘች አገር በመሆኗ በአፍሪካ ኢኮኖሚና ዘላቂ ልማት ላይ የሚጠበቅባትን አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑን ገልጸዋል።   

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ኢትዮጵያ ለጀመረቻቸው የሪፎርም ሥራዎች የሚያግዙ መረጃዎችን ለፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪዎች እያቀበለ መሆኑንም ተናግረዋል።

የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ውሳኔ መስጠት የሚያስችሉ ስታትስቲካዊ መረጃዎች ወሳኝ መሆናቸውንም ገልጸዋል።   

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን ቀሬ በበኩላቸው አገልግሎቱ አዳዲስ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎችን በማዘመን ለኢትዮጵያ የሚመጥን የመረጃ ተቋም ለመሆን እየሰራ ነው ብለዋል።  


 

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና አተገባበርን በመደገፍ ከሚጫወተው ሚና ባሻገር የመረጃ አጠቃቀምን ለዘላቂ ልማት እንዲውል እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።   

አገልግሎቱ ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ስታትስቲክስ ልማት ስትራቴጂ በማዘጋጀት ግንባር ቀደም ሆኖ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።    

የአፍሪካ ስታትስቲክስ ቀን በሁሉም የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የስታትስቲክስ አስፈላጊነት ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የሚፈጠርበት ቀን ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም