ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ አዳዲስ አውሮፕላኖችን ሊገዛ ነው 

አዲስ አበባ፤ህዳር 8/2016 (ኢዜአ)፡-  የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰሞኑን ለመግዛት ሥምምነት ካደረገው 84 አውሮፕላኖችን በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ አውሮፕላኖችን በቅርቡ ለመግዛት በሂደት ላይ መሆኑን ገለጸ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አየር መንገዱ ያስቀመጠውን ራዕይ እውን ለማድረግ የአውሮፕላን ግዥ ሥምምነቱ ተከናውኗል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ከቦይንግና ከኤር ባስ የአውሮፕላን ኩባንያዎች በድምሩ  84 የመንገደኞች አውሮፕላኖች ለመግዛት ሥምምነት መደረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይም በጥናት ላይ የተመሰረተ ተመሳሳይ የአውሮፕላን ትዕዛዞችን ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል። 

እነዚህ አውሮፕላኖች 100 መንገደኞችን መጫን የሚችሉና ለአገር ውስጥና ለጎረቤት አገራት ትራንስፖርት ለማዋል መታቀዱን ጠቁመዋል።

በዚህም ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈጣን እድገትን በመከተል ዓለም ላይ ካሉ 20 ምርጥ አየር መንገዶች መካከል አንዱ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።  

አየር መንገዱ በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም