ኢትዮጵያ ለ122 አገራት የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት እየሰጠች ነው 

አዲስ አበባ፤ህዳር 8/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለ122 አገራት የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት (ቪዛ ኦን አራይቫል) እየሰጠች መሆኑን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ገለጸ።   

የመዳረሻ ቪዛ አንድ ዜጋ በመዳረሻ አገር ለሚኖረው አጭር ቆይታ የሚያገኘው ሲሆን፤ ቪዛውን ለማግኘት የሚያስፈልጉትን ጉዳዮች በአንድ ቦታ የሚጨርስበት ነው።

ቪዛው አንድ ተጓዥ ኤምባሲና የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በመሄድ የሚያወጣውን ጊዜ በማስቀረት አገልግሎቱን በቀላሉ ማግኘት ያስችለዋል።

የመዳረሻ ቪዛ የሚሰጡ አገራት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚገኝ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ይህንኑ አገልግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች። 

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት፤ ከዚህ ቀደም ከውጭ አገራት ለሚመጡ ዜጎች የቱሪስት ቪዛ አገልግሎት በኦንላይን ሥርዓት የሚሰጡበት አሠራር መዘርጋቱን ይገልጻሉ።

ይሁንና የአገልግሎት መስጫ ሥርዓቱ ረዥም ጊዜ የሚወስድና ደንበኞች ቅሬታዎች በማቅረባቸው ሥርዓቱን የማስተካከል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የቱሪስት ቪዛው አሠራር እስኪስተካከል የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎቱን ተደራሽ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።

በዚሁ መሠረት ከመስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለ122 አገራት የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል። 

አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም የነበረውን መጨናነቅና የተንዛዛ አሠራር ማስቀረቱንና ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ አገር ጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን አመልክተዋል።

የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎቱ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም እድገት አስተዋጽዖ እያደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

 የመዳረሻ ቪዛ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማስፋትና መሻሻል እንዲያሳይ ማድረጉን ነው ዋና ዳይሬክተሯ ያብራሩት።  

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም