ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ያሏትን ፀጋዎች በመጠቀም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ህዳር 8/2016 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ያሏትን ፀጋዎች በመጠቀም የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ የሰው ኃብት ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።  

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ከዘርፉ ተዋንያን ጋር ገምግሟል። 

በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪዎችን የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላትና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የክህሎት ሥልጠና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራትና የሥራ ዕድል መፍጠር የመንግሥት የትኩረት መስክ መሆኑን ገልፀዋል። 

በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት ብቻ ለ500 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር 100 ሺህ ወጣቶች የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል። 

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በግምገማ መድረኩ፤ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ ዕድል ፈጠራና ሥምሪት በአዳዲስ እሳቤዎች መመራት የተጀመረበት ዓመት መሆኑን ገልፀዋል።

የአገር ውስጥና የውጭ አገር የሥራ ሥምሪትን ለማቀላጠፍ ዘርፉን በቴክኖሎጂ መምራት ወሳኝ መሆኑ ታምኖበት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

ክህሎት የመወዳደሪያና ኢንቨስትመንት መሳቢያ መንገድ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያን ከገጠሟት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ችግሮች የማውጣት ኃላፊነት ተጥሎብናል ብለዋል። 

ሥራ አጥነት የማክሮ ኢኮኖሚው ፈተና መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ዜጎችን ከዚህ ማላቀቅና ኢኮኖሚውን ማስተካከል ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የተጀመረውን መሠረታዊ ለውጥ ከዳር ለማድረስ የሰው ኃይላችንን ምርታማ ማድረግ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነውም ብለዋል።

በመሆኑም ክህሎትን በማዳበር የምርታማነትን ባህል የሚያጎለብቱ አሠራሮችን በማኅበረሰብ ደረጃ በፍጥነት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ገልፀዋል።

የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት በትብብር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ፤ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራትና ምርታማነትን ማረጋገጥ ቅድሚያ የምንሰጠው ሥራችን ነው ብለዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው፤ የሰው ኃይልን ምርታማነት ለማጎልበት በቅድሚያ በሰዎች ላይ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ብለዋል። 


 

በዚህም ዘመኑ የሚጠይቀውን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ለሚኒስቴሩ ተጠሪ የሆነ የኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል። 

በዚህም ኢትዮጵያ ያሏትን ፀጋዎች ተጠቅሞ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፤ የኢንዱስትሪዎችን በክህሎቱ የዳበረ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም