ቀጥታ፡

በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተገነባ የፕላስቲክ ቧንቧና ኮንዲት ማምረቻ ፋብሪካ ሥራ ጀመረ

አዳማ ፤ኅዳር 8/2016(ኢዜአ)፦በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከ14 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተገነባ ዘመናዊ የፕላስቲክ ቧንቧና 'ኮንዲት' ማማረቻ ፋብሪካ ዛሬ ሥራ ጀመረ።

ፋብሪካውን ያቋቋሙት "ኢ.ዜድ.ኤም ትሬድ ኤንድ ኢንቨስትመንት" የተሰኘ አገር በቀል ኩባንያ "ሪፎ ኢንተርናሽናል'' ከተሰኘው የቻይናው የፕላስቲክ ቧንቧ አምራችና አቅራቢ ኩባንያ ናቸው።

የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ዳርጌ፣ ፋብሪካው የሚያመርታቸው የቧንቧና የፕላስቲክ ምርቶች ከውጭ ከሚገቡት ምርቶች መተካት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን ከመተካት ባለፈ ፍብሪካው ምርቶቹን ወደ ምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገሮች እንደሚልክ አስታውቀዋል።


 

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት አበበ፣ በፓርኩ ያሉ ሁሉም ሼዶች በ13 ኩባንያዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።

በሀገሪቷ የግንባታ ዕቃዎች አቅርቦት ላይ ወሳኝ ሚና ያለው የቧንቧና የፕላስቲክ ማምረቻ ፋብሪካ ዛሬ ሥራ ጀምሯል ብለዋል።

በፓርኩ ሥራ በጀመሩ ሰባት ድርጅቶች ከ8 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰው ባለፉት ስምንት ወራት አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የገቢ ምርቶች በፓርኩ በተመረቱ ምርቶች  መተካታቸውን አስታውቀዋል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ ለኢንቨስትመንት አመቺ የሆነ ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የውሃ፣ መንገድና የኃይል አቅርቦት ጭምር በማመቻቸት ከተማዋን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ለባለሃብቶች አንድ ማዕከል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸው ከተማው አገልግሎት አሰጣጡን ወደ ዲጂታል በማስገባት ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ እንደገለጹት በሀገሪቷ የተገነቡት 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እየገቡበት መሆኑን አስታውቀዋል።

በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ የጀመረው የቧንቧና የፕላስቲክ ቱቦ ማምረቻ ፋብሪካ የዚሁ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ፓርኮቹ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረባቸውን መላካቸውን ተናግረዋል።

ፓርኮቹ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ተኪ ምርቶች በማምረት የውጭ ምንዛሪ ማዳናቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አመልክተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም