ቀጥታ፡

የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤዉን እያካሄደ ነዉ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2016(ኢዜአ):-የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤዉን በአፍሪካ ኅብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ  በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በጉባኤዉ ላይ ከ47 አባል አገራት የ44ቱ አገራት ተወካዮች ተገኝተዋል። 

ጉባኤው የኮንፌዴሬሽኑን ቀጣይ ፕሬዘዳንት በመምረጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት እያሱ ወሰን ለኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንትነት ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።

በጉባኤው የባህልና ስፖርት፤  የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ቦክስ አሶሴሽን ፕሬዝዳንት ኦማር  ክሪምለይ ተገኝተዋል። 

የዓለም አቀፉ ቦክስ አሶሴሸን ፕሬዝዳንት ኦማር ክሪምለይ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት የቦክስ ስፖርት ከእግር ኳስና አትሌቲክስ  ያልተናነሰ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

አለም አቀፉ ማኅበር የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽንን ለመደገፍ ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ገልፀዋል።

በአፍሪካ ለቦክስ ስፖርት ማደግ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ቢፈስም የአሰራር ብልሹነት በመኖሩ ስፖርቱ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ተፅዕኖ በማሳረፉ ይህን ለማስተካከል እንሰራለን ብለዋል።

በአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከአቶ እያሱ በተጨማሪ ከካሜሩን በርትራንድ ሜንዱጋ እና ሞሮኮዊው መሐመድ ኤል ካቡሪ ይወዳደራሉ።

የኮንፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አዛንዚያ ኦሞ-አጌጌ ከናይጄሪያና የዩጋንዳ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሞሰስ ሙሃንጊ ራሳቸውን ከውድድሩ ማግለላቸውን የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን መረጃ አመላክቷል።

ከቀረቡት ዕጩዎች የተሻለ ድምጽ ያገኘው የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት በመሆን ለአራት ዓመት ፌዴሬሽኑን ይመራል።

ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው መራጮች ብቻ በተገኙበት በዝግ እየተከናወነ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም