የጎዴ ከተማ ዜጎች በሕብረ-ብሔራዊነት የሚኖሩባት የሰላም ተምሳሌት ነች - የከተማዋ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ህዳር 8/2016 (ኢዜአ)፡-የሶማሌ ክልል የሸበሌ ዞን መቀመጫ ጎዴ ከተማ ዜጎች በሕብረ-ብሔራዊነት የሚኖሩባት የሰላም ተምሳሌት መሆኗን የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። 

በጎዴ ከተማ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተገነቡ የልማት ሥራዎችም የከተማዋን ገጽታ በመቀየር የነዋሪዎችን ሕይወት ማሻሻል ያስቻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።  

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ የጎዴ ከተማ ዜጎች የቋንቋና የኃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው በፍቅር፣ በመቻቻል፣ በአንድነትና በሰላም የሚኖሩባት ናት። 

ከአሥር ዓመታት በላይ በጎዴ ከተማ የኖሩት ኃይሌ ሐጎስ፤ ጎዴ ከተማ የኃይማኖትና የቋንቋ ልዩነት ሳይገድበን በአንድነትና በፍቅር የምንኖርባት ከተማ ነች ብለዋል። 


 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ፣ የወጣቶች መዝናኛና ሌሎች የመሠረተ- ልማት ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ በመቀየር የነዋሪዎችን ህይወት እያሻሻሉ እንደሚገኙ ገልፀዋል። 

በከተማዋ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ በርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፍቅር በአንድነትና በመቻቻል ኃብትና ንብረት አፍርተው እየኖሩባት መሆኑን አንስተዋል። 

ዘይነባ መሀመድ ጎሹ በጎዴ ከተማ መኖር ከጀመረች አሥር ዓመት እንዳለፋት በመጥቀስ፤ በከተማዋ የተፈጠረው አስተማማኝ ሰላምና ደኅንነት ኑሯቸውን በጥሩ ሁኔታ ለመምራት እንዳገዛቸው ተናግራለች። 

ከዚህ ቀደም ነዋሪዎች ሲቸገሩበት የነበረው የውሃ፣ መብራት፣ መንገድና ሌሎች የመሰረተ-ልማት ግንባታ ሥራዎች እየተሻሻሉ እንደሚገኙ አንስታለች።

የጎዴ ከተማ ወጣቶች ማኅበር አባልና የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ራባ ሸቃሊ በበኩሉ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጎዴ ከተማ ውጤታማ የመሠረተ-ልማት ማስፋፊያ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጿል። 


 

የፌደራልና የክልሉ መንግሥት የከተማዋን የውሃ፣ የመንገድና ሌሎች የመሠረተ-ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እያደረገ ለሚገኘው ከፍተኛ ርብርብ ምስጋና አቅርቧል። 

የከተማዋ ወጣቶች በሚከናወኑ የሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የልማት ሥራዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆናቸውን በማስታወስ፤ በቀጣይም የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል።

በጎዴ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች አበረታች ናቸው ያለው ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አሕመድ ኑር መሃመድ ነው። 

በከተማዋ በመንገድ፣ በውሃ ልማት፣ በትምህርት፣ በመብራት መሠረተ-ልማት ዘርፍ ውጤታማ ሥራ መከናወኑንም ተናግሯል። 

18ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ምክንያት በማድረግ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስተባባሪነት የመስክ ምልከታ ተከናውኗል። 

በዚህም የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች በጎዴ ከተማ የተገነቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ የአረንጓዴ ልማት፣ የውስጥ ለውስጥ የመንገድ መሠረተ-ልማት፣ የጎዴ አየር ማረፊያና የአጠቃላይ ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታ የልማት ሥራዎች ተጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም