መንግሥት የውጪ አገር የሥራ ሥምሪት መዳረሻዎችን ለማስፋት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት የውጪ አገር የሥራ ሥምሪት መዳረሻዎችን ለማስፋት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ህዳር 8/2016 (ኢዜአ)፡-መንግስት የውጪ አገር የሥራ ሥምሪት መዳረሻዎችን ለማስፋት በቅርቡ ከአውሮፓና እስያ አገራት ጋር አዳዲስ ሥምምነቶችን እንደሚፈራረም ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል ለኢዜአ እንደገለጹት መንግሥት የሥራ እድል ፈጠራን ለማስፋት የተለያዩ አማራጮችን በመዘርጋት ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
የውጪ አገር የሥራ ሥምሪት የሥራ እድል ከሚፈጠርባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑ አንስተው ደኅንነቱ የተጠበቀ የውጪ አገር የሥራ ሥምሪት ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ በቅርቡ ከአውሮፓና እስያ አገራት ጋር መሰል ሥምምነቶች እንደሚደረጉ ገልጸው ይህም ለዜጎች የተሻለ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ እድል መሆኑን አስረድተዋል።
ሚኒስትሯ ከመዳረሻ አገራት ጋር የሚደረጉ የሁለትዮሽ ሥምምነቶች የዜጎችን ደኅንነትና መብት ከማስጠበቅ በዘለለ መልካም የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት እንዲፈጠር አድርጓል ይላሉ።
ዜጎች ደኅንነታቸውና መብታቸው ተጠብቆ ሥራ የሚያገኙበትን አማራጭ ለመዘርጋት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ቀደም ሲል በዜጎች ላይ ይደርስ የነበረው የመብት ጥሰት ሪፖርቶች እየቀነሱ መምጣታቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ የሚደረጉ ሥምምነቶቹ ውጤታማ መሆናቸውን ያመለክታል።
በዚህ ረገድ የተመዘገበው ውጤት የሚበረታታ ቢሆንም በሚፈለገውን ደረጃ ላይ ለመድረስ ግን አሁንም በትኩረት መሥራት የሚጠይቅ በመሆኑ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ኳታር፣ ሊባኖስና ጆርዳን ኢትዮጵያ ሕጋዊ የሥራ ሥምሪት ሥምምነት ከተፈራረመቻቸው አገራት መካከል ይጠቀሳሉ።