በሶማሌ ክልል ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያድርጉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያድርጉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2016(ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል በተለያዩ መስኮች ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያድርጉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገለጸ።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት በጅግጅጋ ከተማ የሚከበረው 18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን አስመልክቶ ከመገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ የጋዜጠኞች ቡድን በክልሉ የተገነቡ የመሠረተ-ልማት ግንባታና የልማት ሥራዎችን በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ።
የሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፈርሃን ጅብሪል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የጋዜጠኞች ቡድን የበዓሉን ዝግጅትና የክልሉን የልማት እንቅስቃሴ የሚያደርጉትን ምልከታ መረጃ እንዲያደርሱ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታትም የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ አበይት የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥትም ምቹ የሰላምና ደኅንነት ምህዳርን በመፍጠር ከፌደራል መንግሥት ጋር በመተባበር ቀብሪ ደሀር እና ደገሀቡር ከተሞችን ጨምሮ ከ66 በላይ የሚሆኑ ከተሞችን የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል እንደተቻለ ተናግረዋል።
ዚህ ቀደም በክልሉ የነበረው ሰፊ የመንገድ መሠረተ-ልማትም ዜጎች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ሲፈጥር መቆየቱን መነሻ በማድረግ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በክልሉ መንግሥት በጀት ከተማን ከገጠርና ገጠርን ከከተማ ማገናኘት የሚያስችል ከ2ሺህ 500 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ መገንባት ተችሏል ብለዋል።
በፌደራል መንግሥት ደረጃም ከ7 ቢሊየን ብር በላይ በሚሆን በጀት ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገራት ጋር የሚያገናኝ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ በመሠራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በውሃ ልማት ዘርፍም 19 ከመቶ የነበረውን የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን ወደ 43 ነጥብ 4 በመቶ በማሳደግ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
ጅግጅጋ፣ ጎዴና ቀብሪ ደሀር ከተሞችን ጨምሮ በ13 የክልሉ ትላልቅ ከተሞችንና ሌሎች የገጠር መንደሮችን ሰፋፊ የውሃ መሠረተ-ልማት በማከናወን ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ጠቁመዋል።
በክልሉ የተፈጠረው አስተማማኝ የሰላም ሁኔታም አልሚ ባለሀብቶች በተለያዩ ከተሞችና የልማት ዕድሎች በመሳተፍ እራሳቸውንና ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉበት ዕድል እንደተፈጠረ ጠቅሰዋል።
ከኅዳር 25 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የሚከበረውን የ18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓልን በልዩ ድምቀት ለማክበር የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በበዓሉም የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ የባህል ትርዒቶች፣ ሲምፖዚየምና የምክክር መድረክን ጨምሮ በተለያዩ ሁነቶች የሚከበር መሆኑንም ገልፀዋል።
ወደ ጅግጅጋ ከተማ የሚመጡ እንግዶችም ወደ ሁለተኛ ቤታቸው የሚመጡ መሆናቸውን በመገንዘብ በዓሉን በደስታና በፍቅር እንዲያከብሩ ለማድረግ አስፈላጊ የቅድመ-ዝግጅት ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የዘንድሮው የ18ኛ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል ከኅዳር 25 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት "ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በጅግጅጋ ከተማ ይከበራል።