በሸበሌ ወንዝ ላይ የተሰራው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የጎዴ ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሸበሌ ወንዝ ላይ የተሰራው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የጎዴ ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው
አዲስ አበባ፤ህዳር 8/2016 (ኢዜአ)፡- በሸበሌ ወንዝ ላይ በ475 ሚሊየን ብር የተሰራው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የጎዴ ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን መሆኑን የጎዴ ከተማ ገለጸ።
18 ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ምክንያት በማድረግ በፌደሬሽን ምክር ቤትና በሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስተባባሪነት የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን ጎዴ ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በዚህም የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ የአረንጓዴ ልማት፣ የውስጥ ለውስጥ የመንገድ መሰረተ ልማት፣ የጎዴ አየር ማረፊያና የሆስፒታል ማስፋፊያ የልማት ሥራዎች ተጎብኝቷል።
የሶማሌ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፈርሃን ጅብሪል፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የክልሉን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ የዜጎችን የመሰረት ጥያቄ መልስ መስጠት ያስቻለ የ2 ሺ 700 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ መገንባቱን ተናግረዋል።
በክልሉ የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን በመጥቀስ በሸበሌ ወንዝ ላይ በ475 ሚሊዮን ብር በጀት የተሰራው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ የመስኖ ልማት ስራ፣ የጎዴ አየር ማረፊያና የሆስፒታል ማስፋፊያ ስራዎችን በአብነት አንስተዋል።
የጎዴ ከተማ ከንቲባ አብዱላሂ አሊ ሀጂ፤ የከተማዋን ነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ማሻሻል ያስቻሉ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
ለአብነትም የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የአረንጓዴ ሥፍራና ወጣቶች መዝናኛ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የጎዴ ከተማ ውኃ ልማት ሥራ አስኪያጅ መሃመድ ሰይድ ዲጋሌ፤ በ475 ሚሊየን ብር በጀት የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ለሚቀጥሉት 30 ዓመታት ከ107 ሺህ በላይ የሚሆኑ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
በፌዴራል መንግሥት፣ በዓለም ባንክና በክልሉ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ግንቦት 2011 ዓ.ም የተጀመረው የጎዴ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በሁለት ዓመት ጊዜ ተጠናቆ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀው የውሃ ፕሮጀክትም የከተማዋ ነዋሪዎች ሲያጋጥማቸው የነበረውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር እንደቀረፈ ገልጸዋል።
የጎዴ ጠቅላላ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አብዱ ሀኪም ሳህኔ አብዱላሂ፥ በሆስፒታሉ እየተከናወነ የሚገኘው የማስፋፊያ ሥራ የጤና አገልግሎቱን ተደራሽነት ማስፋት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የሆስፒታሉ የማስፋፊያ ግንባታ የእናቶችና ህፃናትን ጨምሮ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
18ኛ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ከኅዳር 25 እስከ 29/2016 ዓ.ም ድረስ በፌደሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት "ብዝኅነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በጅግጅጋ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት እንደሚከበር የተያዘው መርኅ-ግብር ያመላክታል።