በሶማሌ ክልል ቀብሪ ደሀር ከተማ የከተማዋን ገጽታ መቀየር ያስቻሉ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ቀብሪ ደሀር ከተማ የከተማዋን ገጽታ መቀየር ያስቻሉ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2016(ኢዜአ):-በሶማሌ ክልል የቀብሪ ደሀር ከተማ ከለውጡ በኋላ የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ በርካታ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።
18ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ምክንያት በማድረግ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስተባባሪነት የተዘጋጀ የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች ቡድን የሶማሌ ክልል የልማት ሥራዎች ምልከታ በቀብሪ ደሀር ከተማ ቀጥሏል።
የጋዜጠኞች ቡድኑም በቀብሪ ደሀር ከተማ የተከናወኑ የወጣቶችና የአረንጓዴ ልማት፣ የውስጥ ለውስጥ የመንገድ መሠረተ-ልማት እስከ 50 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የ90.8 የሬዲዮ ጣቢያ ግንባታና ሌሎች የመሰረተ-ልማት ማስፋፊያ ግንባታ ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
የቀብሪ ደሀር ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር አብዱረዛቅ አወል፤ ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ የከተማዋን ገጽታ መቀየር ያስቻሉ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የእግረኛ፣ የውስጥ ለውስጥና የአስፋልት መንገድ መሠረተ-ልማትን ጨምሮ የውሃ፣ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የወጣቶች መዝናኛና ሌሎች ውጤታማ የልማት ሥራዎችን በማልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደተቻለ ተናግረዋል።
የቀብሪ ደሃር ከተማ ሥራአስኪያጅ ኢንጂነር አሊ መሃመድ በበኩላቸው፤ ከተማዋን ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ ያስቻሉ የመሠረተ-ልማት ግንባታ ተከናውነዋል ብለዋል።
ለአብነትም ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የተሻለ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክና የውሃ መሠረተ-ልማት ግንባታ መከናወኑን ገልፀዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም የከተማዋን ወጣቶች በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለማድረግ የንግድ ቦታ ሼድ ግንባታ መከናወኑን ተናግረዋል።
በ2015 በጀት ዓመትም በአጠቃላይ 7 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን በማደራጀት በእንጨት ሥራ፣ በንግድ እና ሌሎች ዘርፎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውቀዋል።
በሆቴል ቱሪዝም አገልግሎት፣ በአምራች ኢንዱስትሪ እና ሌሎች ዘርፎች መሰማራት የሚሹ አልሚ ባለሀብቶች በሚፈልጉት መስክ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የከተማዋን አመራርና ፈጻሚ በማቀናጀት የሕዝብን ጥያቄ መልስ የሰጡ የልማት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቀብሪ ደሃር ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብዲሂላል አብዲ ናቸው።
በከተማዋ የተከናወኑት የልማት ሥራዎችም የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በቀጣይም ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በትኩረት መሥራት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓትና ተነሳሽነት መፈጠሩን አንስተዋል።
የዘንድሮው የ18ኛ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል ከኅዳር 25 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት "ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በጅግጅጋ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።