ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የመደመር እሳቤን መሰረት በማድረግ ከራሷ ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር የሚወሉ መሰረተ ልማቶችን እያከናወነች ነው - ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2016(ኢዜአ):-ኢትዮጵያ የመደመር እሳቤን መሰረት በማድረግ ከራሷ ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር የሚወሉ መሰረተ ልማቶችን እያከናወነች መሆኑን የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ ገለጹ።

የድሬዳዋ አስተዳደርና ኢዜአ በመተባበር ''መደመር ለቀጣናዊ ብልጽግና '' በሚል መሪ ሃሳብ  ያዘጋጁት ምእራፍ ስድስት የመደመር ጉዞ ፓናል ውይይት በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩም የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀርን ጨምሮ የፌደራልና የድሬደዋ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በፓናል ውይይቱ የነዳጅና ኢነርጂ ባልስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ “መደመር መሰረተ ልማቶችና ቀጣናዊ ትስስር” በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መነሻ ሃሳብ አቅርበዋል።

በዚህም የመደመር እሳቤ ለጋራ ልማት በጋራ መቆም እንደሚገባ የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከቀጣናው አገራት ጋር በመንገድ፣ በሃይልና በሌሎች የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ለመተሳሰር እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ የድሬደዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ተጨማሪ እድል ይዞ መምጣቱንም አውስተዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ከፉክክር ይልቅ ትብብርን መሰረት ያደረገ ትስስር እንድትፈጥር አድርጓል ነው ያሉት።

አሁን ላይም ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የኢነርጂ ማዕከል ለመሆን እየሰራች እንደምትገኝም ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

ይህም የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር በቱሪዝም ተጨማሪ ገቢ እንድታገኝ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም