ከ114 ቶን በላይ የምግብ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ከ114 ቶን በላይ የምግብ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2016(ኢዜአ):-በበጀት ሩብ ዓመቱ የምርት ጥራት ጉድለት የተገኘባቸው ከ114 ቶን በላይ የምግብ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረጉን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ገለጸ።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ስዩም ወልዴ፤ የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በተለያዩ ምርቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።
በሩብ ዓመቱ በተደረጉ የቁጥጥር ሥራዎች የምርት ጥራት ጉድለት የተገኘባቸው ከ114 ቶን በላይ የምግብ ምርቶች ወደ አገር እንዳይገቡ መደረጉን ጠቁመዋል።
እነዚህ የምግብ ምርቶች የተቀመጠውን መስፈርት ባለማሟላት፣ የምርት ጥራት ጉድለት ስለተገኘባቸውና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው በማለፋ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
የምግብ ምርቶቹ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የተደረገው በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግማሾቹ ምርቶች ወደ መጡበት አገር እንደተመለሱ ቀሪዎቹ ደግሞ መወገዳቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ግምታቸው ከ53 ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ የምግቦች ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጓል ነው ያሉት።
በአንፃሩ በአገልግሎቱ የተቀመጡ መስፈርቶችን በማሟላት ጥራታቸው የተረጋገጠ ከ736 ሺህ ቶን በላይ ምግቦች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉንም አብራርተዋል።
በተመሳሳይ የጥራት መስፈርት ያሟሉና ግምታቸው ከ470 ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ የውበት መጠበቂያዎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።
በአንፃሩ ከ465 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡና የጥራት ፍተሻውን ማለፍ ያልቻሉ የውበት መጠበቂያ ቁሳቁሶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረጉንም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በሩብ ዓመቱ በመድኃኒት ዘርፍ 195 ለሚጠጉ የመድኃኒት ተቋማት ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸው፤ 319 የሚጠጉ የምግብ ተቋማት ደግሞ ፈቃድ ማግኘት መቻላቸውን ገልፀዋል።
በምዝገባ በኩል ደግሞ 160 የሚጠጉ መድኃኒቶችና 619 ምግቦች እንዲሁ ምዝገባ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል።