በሦስት ወራት ውስጥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ383 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በሦስት ወራት ውስጥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ383 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2016(ኢዜአ):-በሦስት ወራት ውስጥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ383 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የተቋሙ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም በተያዘው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት በአንደኛ ሩብ ዓመት ለግድቡ ግንባታ ከኅብረተሰቡ ገቢ ለመሰብሰብ ልዩ ልዩ የገቢ ማሰባሰበያ መንገዶች ተግባራዊ ሲደረጉ ቆይተዋል ብለዋል።
በዚህም ከ383 ሚሊየን በላይ ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን አረጋግጠዋል።
ይህንንም ተከትሎ ከአገር ውስጥ ቦንድ ሽያጭና ስጦታ 273 ሚሊየን 960 ሺህ ብር በላይ ከዳያስፖራ ቦንድ ሽያጭና ስጦታ 4 ሚሊየን 31 ሺህ ብር በላይ ተገኝቷል ብለዋል።
በተጨማሪም ከ8100 ኤ አጭር የሞባይል የጽሁፍ መልዕክት አገልግሎት 33 ሚሊየን 802 ሺህ ብር በላይ እንዲሁም ከፒን ሽያጭ 352 ሺህ ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥጦታ አካውንት ገቢ የሆነ 71 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑንም እንዲሁ።
ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ በየጊዜው እያደረጉ ያለውን የነቃ ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉም አቶ ሀይሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የግድቡ ግንባታ መሰረት ድንጋይ ከተጣለ አንስቶ እስካሁን 18 ቢሊየን 613 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።