የመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ እውነተኛ ህብረ - ብሔራዊ ፌደራሊዝምን እውን ከማድረግ ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር መሰረት የጣለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ እውነተኛ ህብረ - ብሔራዊ ፌደራሊዝምን እውን ከማድረግ ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር መሰረት የጣለ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2016(ኢዜአ):- የመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ እውነተኛ ህብረ - ብሔራዊ ፌደራሊዝምን እውን ከማድረግ ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር መሰረት የጣለ መሆኑን የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር ገለጹ።
የድሬዳዋ አስተዳደርና ኢዜአ በመተባበር ያዘጋጁት "የመደመር ጉዞ'' የፓናል ውይይት በድሬዳዋ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
የፓናል ውይይት መድረኩ ''መደመር ለቀጣናዊ ብልጽግና '' በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ሲሆን፤ የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀርን ጨምሮ የፌደራልና የድሬደዋ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የመደመር እሳቤ አገር በቀል እውቀቶችን መሰረት ያደረገና ኢትዮጵያዊያን የበለጸገች አገር ለመገንባት በጋራ እንዲሰሩ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
እሳቤው በሁሉም አካባቢዎች ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የህይወት ዘይቤ ጋር የሚጣጣም መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ የጥላቻና መጠላለፍ ፖለቲካን አስወግዶ እውነተኛ ህብረ-ብሄራዊ ፌደራሊዝም እውን እንዲሆን መሰረት የጣለ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
በተጨማሪም የመደመር እሳቤ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ በሰጠ ዲፕሎማሲ የተቃኘ በመሆኑ ቀጣናዊ ትስስር እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ነው የተናገሩት።
ድሬዳዋ ደግሞ በቀደመ ታሪኳና ማህበራዊ መስተጋብሯ ሁሉንም ማንነቶች በማስተናገድ ለቀጣናዊ ትብብር ማእከል ሆኗ እያገለገለች መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ መደመር ለችግሮቻችን ዘመኑን የዋጀ መፍትሄ እንዲመጣ አቅጣጫ ያሳየ እሳቤ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ትውልዱ ከጎረቤት ብሎም ከአፍሪካ አገራት ጋር ጠንካራ ትስስር እንዲኖር በሃላፊነት እንዲሰራ መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።
ኢዜአ አገር በቀል እውቀቶችን መሰረት ያደረገው የመደመር እሳቤ ላይ የተላያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲወያዩ እያከናወነ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።