የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአገራዊ ምክክሩ ዙሪያ ከዳያስፖራዎች ጋር እየተወያየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአገራዊ ምክክሩ ዙሪያ ከዳያስፖራዎች ጋር እየተወያየ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2016(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን "የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሚናና ተሳትፎ ለአገራዊ ምክክርና ለአገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ኃሳብ ከዳያስፖራ አባላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ ጊዜ፤ ኮሚሽኑ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅትና የተሳታፊዎች ልየታ ጨምሮ ሌሎች ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የዳያስፖራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ዳያስፖራው በምክክሩ ተሳትፎውን ማጠናከር አለበት ብለዋል።
በምክክሩ ሂደቱ ዳያስፖራው የበኩሉን ተሳትፎ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆን ዳያስፖራው ባለው እውቀት የኮሚሽኑን ሥራ ሊደግፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዳያስፖራው የአገራዊ ምክክሩ ሥራ እንዲሳካ ተሳትፎውን እንደሚያጠናክር የገለጹት ደግሞ ዲያስፖራውን በመወከል ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማኅበር አባል የሆኑት ካፒቴን ሰለሞን ግዛው ናቸው።
በምንችለው ሁሉ የአገሪቱ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ዳያስፖራው እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካና የኃሳብ መሪዎች መካከል እጅግ መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የኃሳብ ልዩነትና አለመግባባት ላይ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር እየሰራ ነው።
አካታች አገራዊ ምክክሮችን ማካሄድ የተሻለ አገራዊ መግባባትን ለመገንባት በሂደትም የመተማመንና ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ለማጎልበት መቋቋሙ ይታወሳል።