በምዕራብ ሸዋ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ ተሸጠ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ ተሸጠ
አምቦ ህዳር 8 / 2016(ኢዜአ)፦በምዕራብ ሸዋ ዞን ባለፉት አምስት ቀናት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ ሽያጭ መከናወኑን የዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ወርቅነህ ሁንዴሳ ለኢዜአ እንዳስታወቁት የዞኑ ሕዝብ ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።
በተያዘው ዓመት በዞኑ 45 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ በተደረገው እንቅስቃሴ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው ቦንድ መሸጡን ነው የገለጹት፡፡
በዞኑ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት እየተካሄደ ሲሆን ከህዳር 03 እስከ 07 ቀን 2016 ዓ.ም በተደረገ እንቅስቃሴ የቦንድ ሽያጩ መከናወኑንም ጠቁመዋል።
በየደረጃው ያለው አመራር የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ያለውን ሀገራዊ ፋይዳ በመረዳት ኅብረተሰቡን በማስተባበር አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የዞኑ ህብረተሰብ የግድቡን ግንባታ በገንዘብ ለመደገፍ በቦንድ ሽያጩ በንቃት እንዲሳተፍ ተወካዩ ጠይቀዋል።
የአምቦ ከተማ ነዋሪው አቶ ሙሉቀን አባተ በሰጡት አስተያየት ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ እንዲውል ቀደም ሲል የ5 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰው፣ አሁን ላይም የ3 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡
ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ህዝቡን በማነሳሳት ድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑንና የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል፡፡
ሌላዋ የዚሁ ከተማ ነዋሪዋ የመንግሥት ሠራተኛ ወይዘሮ ወይንሸት ማሩ የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያን ወደ እድገትና ብልጽግና ጎዳና የሚያሸጋግር በመሆኑ ኅብረተሰቡ በቦንድ ግዢ እንዲሳተፍ ጠይቀዋል፡፡
በግላቸው ከዚህ በፊት የገዙት ቦንድ ከነወለዱ ተመላሽ እንደሆነላቸው ገልጸው፣ በዚህ ሣምንት የሁለት ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸዋል።
''የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የልማት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ የአንድነት ተምሳሌትና የሉዓላዊነት ምልክት በመሆኑ ቦንድ መግዛት ይጠበቅብናል'' ያሉት የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ አበራ ጫላ ናቸው፡፡
ከዚህ በፊት ቦንድ በመግዛት ያደረጉትን ተሳትፎ ሰሞኑንም የ20 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት ማጠናከራቸውን አስታውቀዋል። የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድጋፋቸው እንደሚቀጥል በማረጋገጥ።
የምዕራብ ሸዋ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች፣ ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች እስካሁን ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከቦንድ ሽያጭና በስጦታ ከ145 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።