ቀጥታ፡

አንድነትን የሚያጠናክር አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት አገራዊ ምክክር ወሳኝ በመሆኑ ተሳትፏችን ሊጠናከር ይገባል - የፖለቲካ ፓርቲዎች

 አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2016(ኢዜአ):-በኢትዮጵያ አንድነትን የሚያጠናክር አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት አገራዊ ምክክር ወሳኝ በመሆኑ ተሳትፏችን ሊጠናከር ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የህዝብን አንድነት የሚያጠናክር አሰባሳቢ ትርክት መገንባት ላይ በአግባቡ ባለመሰራቱ ዜጎች በተለያዩ ጊዜያት ዋጋ ሲከፍሉ ቆይተዋል።

ልዩነቶችን ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ መፍታት አለመቻል ዜጎችን ለሞት፣ ለመፈናቀልና ለንብረት ውድመት ሲዳርጋቸው ይስተዋላል።

የኔ ኃሳብ ብቻ ነው ትክክል የሚለው ነጠላ ትርክትም እንዲሁ በትውልዱ ዘንድ ቀውስን እያባባሰ ያለ ችግር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንዳሉት በኢትዮጵያ በወል ዕውነቶች ላይ የተመሰረተ አሰባሳቢ ትርክት መገንባት ይገባል።    

ለዚህ ደግሞ የምሁራን፣ የፖለቲካ ሊሒቃን፣ የመንግሥትና ሕዝብ ኃላፊነት የላቀ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባል ዶክተር መብራቱ ዓለሙ፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላምና አንድነት ለማስፈን ከጥላቻና መገፋፋት ፖለቲካ መውጣት እንደሚገባ ገልጸዋል። 

በሰንደቅ ዓላማ ሆነ በታሪክ ትርክት ለምን እንጋጫለን ያሉት ዶክተር መብራቱ  በጉዳዮች ላይ ተከራክረን፣ ተነጋግረን ተወያይተን ለአገር የሚበጅ  መፍትሄ ላይ መድረስ አለብንም ነው ያሉት። 

አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም አሰባሳቢ ትርክት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ ሁላችንም ተሳትፏችንን ልናጠናክር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ምሁራንም የሚያቀራርቡ ኃሳቦች ላይ ትኩረት በማድረግ በኩል ለአገራዊ አንድነት መጠናከር የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። 


 

የሕብር ዲሞክራሲ ፓርቲ አባል ጸገነት ተስፋዬ በበኩላቸው ጊዜው ትውልዱ ቆም ብሎ ሊያስብ የሚገባበትና ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ የምንፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ከጠቃሚ ትርክቶች ይልቅ ጎጂ ትርክቶች ቦታ እየያዙ በመምጣታቸው ዋጋ እየከፍልን ነው ያሉት ወይዘሮ ጸገነት ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ነገን መፍጠር የኛ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት ምክክርን ያስቀደመ አካሄድ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።  

በጎጂ ትርክቶች ምክንያት የሚስተዋሉ ችግሮችን በማስቀረት ለጋራ ጉዳይ በጋራ የመሥራት ባህልን ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም