አብሮነታችንን የሚገነቡ ገዢ ትርክቶችን በማስፋት የለማችና የፀናች ሀገር ለትውልድ የማውረስ ሃላፊነት አለብን-የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
አብሮነታችንን የሚገነቡ ገዢ ትርክቶችን በማስፋት የለማችና የፀናች ሀገር ለትውልድ የማውረስ ሃላፊነት አለብን-የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች
አርባ ምንጭ ፤ ህዳር 7/2016(ኢዜአ)፦ አብሮነታችንን የሚያጠናክሩና ሀገርን የሚገነቡ የጋራ ትርክቶችን በማስፋት የለማችና የፀናች አገር ለትውልድ የማውረስ ሃላፊነት አለብን ሲሉ የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች አመለከቱ።
የጋሞ አባቶች በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ግጭቶችን በእርጥብ ሳር በማብረድ በሰላም ተምሳሌትነት ይታወቃሉ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች እንዳሉት፤ የእርስ በርስ ግንኙነታችንን በጠንካራ መሰረት ላይ በማጽናትና አንድነታችን በመጠበቅ የለማች አገር ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ሃላፊነት አለብን።
ትናንት የተሰሩ ስራዎች ለዛሬ ልማትና ጥፋት ምክንያት እየሆኑ እንዳሉ ሁሉ ዛሬ ላይ የምንሰራቸውና የምንገነባቸው ትርክቶች ለመጪው ትውልድ ጠንካራ አብሮነት ሚናቸው ይልቃል በማለት ገልጸዋል።
በመሆኑም ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የአባትነትና የዜግነት ሃላፊነትን መወጣት አለብን ብለዋል።
ከአባቶቹ መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ተፈራ ኦይቻ ቀደምት አባቶቻችን አንድነታቸውን በማጠንከር በአድዋ ጀግንነት ያስመዘገቡት የጋራ ትርክት በዓለም የጥቁሮች ቀንዲል ሆኖ ከመመዝገቡም በተጨማሪ ለሀገራችን መጽናት ትልቅ ድርሻ እንዳለው አውስተዋል።
ዛሬም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝቡ ከዳር እስከ ዳር በመረባረብ በልማቱ ረገድ ሌላ ሀገራዊና ገዢ ትርክት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል።
የትናንቱ ለዛሬ እንደሆነ ሁሉ የዛሬው ለነገ ትውልድ መገለጫው እንደሚሆን ያነሱት አቶ ተፈራ እነዚህን ለአብሮነትና ለአንድነት መጠናከር አቅም የሆኑ የጋራ ዕሴቶችን በማጎልበት ሀገራችንን ማጽናትና ማበልጸግ ይገባናል ሲሉም አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚስተዋሉ ነጠላ ትርክቶች አብሮነታችንና የሀገራችን ዕድገት እየጎዱ የመጪውን ትውልድ መሠረት እየናዱ በመሆናቸው ልብ ልንላቸውና ልንመክታቸው ይገባል ብለዋል።
እንደ አቶ ተፈራ ገለጻ በሀገራችን የተመዘገቡ ለውጦች የጋራ እንደ መሆናቸው መጠን ችግሮችም የጋራ ውጤቶች ናቸው ።
በመሆኑም ችግሮችን በማጉላት ከማባባስ ይልቅ የችግሮችን መሰረታዊ ምክንያትና ምንጭ በመረዳት መፍትሄ ለመስጠት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት ነው ያሉት ።
ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ ለመፈለግ እንደሀገር የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ለዚሁ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አንስተው እንደየባህላችን በመመካከርና በመነጋገር ችግሮቻችንን ነቅሰን በማውጣት ጠንካራ የሆነ የጋራ ሰላም መገንባት ይገባናል ብለዋል።
ቀደምት አባቶቻችን የውስጥ ጉዳዮቻቸውን በመነጋገር በመፍታት እንዲሁም ለውጭ ጠላት ያለምንም ልዩነት በጋራ ምላሽ በመስጠት ይህችን ሀገር ጠብቀው አስረክበውናል ያሉት ሌላኛው የጋሞ የአገር ሽማግሌ አቶ መንግስቱ ደምሴ ናቸው ።
ይህ ከዓለት የጠነከረ አንድነታቸው ከኛ አልፎ ለመላው ዓለም በኩራት የምትጠራ አገርን ማቆየቱን ጠቅሰው ጥቃቅን ችግሮችን በማንሳት ትውልዱ እንዲወዛገብና አንድነታችን እንዲሸረሸር እየተሰሩብን ያሉ ትርክቶች ማውገዝ ይገባል ብለዋል ።
ኢትዮጵያ የምትታወቀው በአንድነት፣ በአብሮነት፣ በጀግንነትና በይቅር ባይነት ነው ያሉት አቶ መንግስቱ ኋላቀር እና ያለፉ ጥቃቅን ነገሮችን እያነሳን የሀገራችንን ሰላምና ልማት ከመጉዳት የምንወጣበት ጊዜ አሁን እንደሆነም ተናግረዋል።
የጋሞ ማህበረሰብ የሰላም ተምሳሌትነት እየጠነከረ እንዲሄድ ወጣቱ ትውልድ ባህሉን እንዲያውቀው ከቤተሰብ ጀምሮ ማስተማር እንደሚገባም ገልጸዋል።