የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን ያዘለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን ያዘለ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን ያቀፈ በመሆኑ ትውልዱ ዋነኛ አጀንዳ ሊያደርገው እንደሚገባ ተመላከተ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ "ፍትኃዊ የወደብ አጠቃቀም ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ልማት" በሚል መሪ ኃሳብ ልዩ ሴሚናር በዛሬው ዕለት አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ወደቦችን የመጠቀም ፍላጎት ከጂኦ-ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሕግና ዲፕሎማሲ አኳያ ጽሑፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ዶክተር በለጠ በላቸው፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከስትራቴጂካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ደኅንነት መስኮች አኳያ ተገቢነት ያለው መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት፣ የኢኮኖሚ አቅምና የእድገት ፍላጎት አንጻር የባህር በር የሌላት አገር መሆኗ የሚያስቆጭ ነው ብለዋል።
ጥያቄው ወደ ሥራ እንዲገባም ይህንን ማድረግ የሚችል ትውልድ መገንባት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዋናነት ጥያቄው መነሳቱ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ትውልዱ ጉዳዩን አጥብቆ እንዲይዘው በር ከፋች መሆኑን አመላክተዋል።
በጉዳዩ ላይ ኢኮኖሚያዊ ምልከታቸውን ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሎጂስቲክስና ሰፕላይስ ማኔጅመንት ተመራማሪው ዶክተር ማቴዎስ እንሰርሙ፤ ወደብ ለአንድ አገር የወጪና የገቢ ንግድ የጀርባ አጥንት ነው።
ለኢኮኖሚ ልማት አስቻይ አቅም መሆኑንም ጠቅሰው፤ ቀጣይነት ያለውን እድገት ለማረጋገጥ የወደብ ጉዳይ ወሳኝ እንደሆነም አብራርተዋል።
በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ አማራጭ ወደብ መጠቀምን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ጥያቄው ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን በበርካታ ምሁራን ቀደም ሲል ጉዳዩ ምርምሮችና ጥናቶች የተደረጉበት መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የረዥም ጊዜ የታሪክ መሠረት እንዳለው የገለጹት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ተደራዳሪ ቡድን አባል አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ ናቸው።
ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ሰፊ የዲፕሎማሲ ውይይቶችን ከአገራት ጋር ማድረግ እንደሚጠበቅባት ጠቁመዋል።
እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጉዳዩ ውይይቶችን በማዘጋጀት ሳይንሳዊ ምክረ-ኃሳቦችን ማፍለቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የቀጣናው አገራት ምሁራን ለመንግሥታት ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች መሠረት የሚጥሉ ተከታታይ ምክክሮችን በማድረግ የመፍትሔ አማራጮችን እንዲያመላክቱም ጠይቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የተነሳው ጉዳይ ለኢትዮጵያ እጅግ በጣም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ መሰል መድረኮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልፀዋል።