የዘንድሮው የብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው የብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዳማ፤ ህዳር 7/2016(ኢዜአ)-የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል የእርስ በርስ ግንኙነትን በሚያጠናክርና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎላ መልኩ እንደሚከበር ፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።
በበዓሉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የሚያስተዋውቁ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡበትም ተገልጿል።
በምክር ቤቱ የመንግሥታት ግንኙነት፣ ብዙኃነትና ዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዳይሬክተርና የበዓሉ የድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ትግሉ መለሰ ለኢዜአ እንደገለጹት የዘንድሮውን በዓል በተሻለ መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በዓሉ በሕገ መንግሥቱና በኅብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ላይ የዕውቀት፣ የግንዛቤና አመለካከት ብዥታዎችን በሚያጠራ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅቱ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል
ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባትና ብዙኃነትን በሚያጠናክሩ በተለይም የብሔሮች ማንነት፣ ባህል፣ የአኗኗርና አመጋገብ ዘይቤ፣ ቁሳቁስና አልባሳት ጭምር እንደሚቀርቡበት አቶ ትግሉ አስታውቀዋል።
በዚህም የህዝቦች ትውውቅ፣ ትስስር፣ አብሮነትና መቻቻልን የሚያጠናክሩ ክንውኖች ይከናወናሉ ብለዋል።
ለበዓሉ በፌዴራል ደረጃና በዓሉን በሚያስተናግደው በሶማሌ ክልል ዞኖች፣ ከተሞችና ወረዳዎች ድረስ ዐቢይና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
''በዓሉ ከመጪው ህዳር 25 እስከ 29/2016 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ኩነቶች ይከበራል'' ያሉት አስተባባሪው፣ ለዚህም ለእያንዳንዱ ቀናት ስያሜ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በዚህም ህዳር 25 ''የወንድማማችነት ቀን'' ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፣ ንግድና ባዛር እንደሚከፈት ገልጸዋል።
''የብዝኃነት ቀን'' ተብሎ በተሰየመው ኅዳር 28 ደግሞ ከ76 ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተውጣጡ የባህል ቡድኖች የሚሳተፉበት ኤግዚቢሽን የሚከፈትበትና የጎዳና ላይ ሩጫ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
ህዳር 27 ''የአብሮነት ቀን'' ሆኖ የተሰየመ ሲሆን፣ የክልሎች የቱሪዝምና የተፈጥሮ ሀብቶች የሚተዋወቁበት ዕለት መሆኑን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ህዳር 28 ''የመደመር ቀን'' ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ምሁራንና የተጋባዥ እንግዶች የሚሳተፉበት ፎረም ይካሄዳል ብለዋል።
'የኢትዮጵያውያን ቀን'' ተብሎ በተሰየመው ኅዳር 29 በዓሉ በድምቀት በተለያዩ ትርዒቶች እንደሚከበር አቶ ትግሉ አስታውቀዋል።
የሶማሌ ክልል የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ተወካይና የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል አቶ ግዛው ደበላ በበኩላቸው በክልሉ በዓሉን ለማክበር አስፈላጊውን ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በየሴክተሩ የተለያዩ ኮሚቴዎችና ንዑሳን ኮሚቴዎች እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ ተዋቅረው እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ብለዋል።
በዚህም ቢሮው ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመሆን በዓሉን መሰረት ባደረገ መንገድ ለማክበር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ከክልሉ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ከ4 ሺህ በላይ እንግዶችና የባህል ቡድኖች በበዓሉ ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ግዛው ገልጸዋል።
ጅግጅጋ የምታስተናግደው የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል የሚከበረው ለ18ኛ ጊዜ ነው።