አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ ሰነድ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ ሰነድ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016(ኢዜአ)፦አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ ሰነድ መዘጋጀቱን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የፍትሕ ሚኒስቴር አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ ሰነድ ላይ ከሚመለከታቸው የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል፡፡
አገር አቀፍ የተቀናጀ ወንጀል መከላከል ስትራቴጂ በሀገርና ህዝብ ሰላም፣ ደህንነትና ጥቅም ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በመከላከልና በመቀነስ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስጠበቅ በ2012 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀ ነው።
ስትራቴጂው የሽብር፣ በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ፣ ከባድ የኢኮኖሚና ከገንዘብ ጋር ተያይዘው የሚፈጸሙ፣ ግድያና ውንብድና፣ በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ፣ የሙስና፣ በሰው የመነገድና ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር፣ የመንገድ ትራፊክ ህግ ጥሰት እና በዜጎች ሰላምና ደህንነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በቅንጅት ለመከላከል የሚያስችል ነው።
እነዚህ ወንጀሎች ውስብስብና ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው ቀድሞ ለመከላከል የተለያዩ ተቋማት በጋራ መስራት የሚያስችል ወጥ የማስፈጸሚያ ሰነድም መዘጋጀቱንም ፍትሕ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ወንጀል የዜጎችን መሰረታዊ ህይወት በማናጋት የሀገርን ህልውና የሚፈታተን ማህበራዊ ተግዳሮት ነው።
ወንጀልን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም አስቀድሞ በመከላከል የሚያደርሰውን ጉዳት መቀነስ እንደሚቻል ተናግረዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ የወንጀል ድርጊቶችን ቀድሞ ለመከላከል በሚኒስትሮች ምክር ቤት አማካኝነት አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከያ ስትራቴጂ በ2012 ዓ.ም ማጽደቋን አስታውሰዋል።
ስትራቴጂው በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሳይሆን የቆየ መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን ላይ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ትብብር በመፍጠር ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የማስፈፀሚያ ሰነድ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ፤ ወንጀል ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ሳይለይ፤ ድንበር ሳይበግረው በማንኛውም ጊዜና ቦታ ሊፈጸም የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ወንጀልን አስቀድሞ መከላከል እና ሲከሰት ደግሞ የጎላ ጉዳት ሳይደርስ ለማስወገድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሉም ማህበረሰብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በውይይቱ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ ወንጀልን መከላከል ለጸጥታ አካላት ብቻ የሚተው ስራ አይደለም ብለዋል፡፡
አገር አቀፍ የተቀናጀ ወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ ሰነድ ውጤታማ አተገባበር እንዲኖረው ሁሉም አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወንጀልን አስከፊነትና የመከላከያ ስልቶችን በተመለከተ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ይገባል ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በየደረጃው ባሉ የትምህርት ተቋማት የግብረ ገብነት ትምህርትን በመጀመር በታዳጊዎች ላይ በመሰረታዊነት ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት እተደረገ መሆኑን ገልጸዋል