ኢትዮጵያ "የሬድ ፕላስ" ምዕራፍ ሁለት የደን ልማት የኢንቨስትመንት ፕሮግራምን ይፋ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ "የሬድ ፕላስ" ምዕራፍ ሁለት የደን ልማት የኢንቨስትመንት ፕሮግራምን ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በ40 ሚሊዮን ዶላር የሚተገበር "የሬድ ፕላስ" ምዕራፍ ሁለት የደን ልማት የኢንቨስትመንት ፕሮግራምን ይፋ አደረገች።
ኢትዮጵያ በደን ልማትና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ እያደረገች ያለውን ጥረት ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ እንዲደግፍ የግብርና ሚኒስቴር ጠይቋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ስቴይን ክሪስቴንሰን፣ የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማምና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ እንዳሉት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 32 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች ተተክለዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚደረገውን ጥረት እየደገፈች መሆኗንና ለዚህም የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀርፃ እየተገበረች መሆኑን ተናግረዋል።
የሬድ ፕላስ የደን ልማት የመጀመሪያው ምዕራፍ መርኃ ግብርም በምግብ፣ በብዝሃ ህይወትና ሌሎችም ዘርፍች ውጤት መምጣቱን ገልጸው፤ በሁለተኛው ምዕራፍም የላቀ ውጤት ይጠበቃል ብለዋል።
በደን ልማት እንክብካቤ ስራዎች ላይ የአጋር አካላት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ሚና እንዳለው በማንሳት፤ በዚህ ረገድ የኖርዌይ መንግስት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ለሌሎች አገራት ምሳሌ እንደሆነ አንስተዋል።
መንግስት ለፕሮግራሙ አተገባበር አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ ሌሎች አካላትም በደን ልማት ላይ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም ሁለቱ አገራት ከ1947 የጀመረ ወዳጅነት እንዳላቸው በማስታወስ የኖርዌይ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ሲሰራባቸው ከቆዩ ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኖርዌይ መንግስት የፕሮጀክቱን የመጀመሪያ ምዕራፍ ትግበራ ሲደግፍ እንደነበር በማስታወስ፤ ይህም የተጎዱ መሬቶችን በደን በመሸፈን እንዲያገግሙ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ስቴይን ክሪስቴንሰን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት እየደገፈን ነው ብለዋል።
ሁለቱ አገራት በአየር ንብረት ዙሪያ በትብብር ለመስራት ከ10 ዓመት በፊት ስምምነት ማድረጋቸውን በማስታወስ፤ የኖርዌይ መንግስት በኢትዮጵያ የደን ልማት ስራን ለመደገፍ እስካሁን 130 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
"የብሄራዊ ሬድ ፕላስ" ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስ እንዳሉት፤ ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ የሬድ ፕላስ ምዕራፍ አንድ በኖርዌይ መንግስትና በሌሎች አጋር አካላት ድጋፍ መተግበሩን ተናግረዋል።
የኖርዌይ መንግስት ለመጀመሪያው ምዕራፍ ትግበራ የ75 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አንስተው ይህም ህብረተሰቡን ያሳተፈ የደን አስተዳደር ለመዘርጋት ያስቻለ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም አንድ ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት እንዲያገግም፣ ወደ ደን እንዲለወጥና እንዲለማ መደረጉ፣ የህብረተሰቡን ህይወት የሚያሻሽሉ የተለያዩ የገጠር ልማት ስራዎች መሰራታቸውንም ነው ያስረዱት።
ለሶስት ዓመታት በሚተገበረው ምዕራፍ ሁለት "የሬድ ፕላስ" ትግበራ 40 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፤ ኖርዌይ 25 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ የሬድ ፕላስ ብሔራዊ የደን ልማት ፕሮግራምን ወደ ካርቦን ገበያ ስርዓት በማስገባት ፕሮግራሙን በራሱ ገቢ በቀጣይነት ለመተግበር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
መርሃ ግብሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በካርቦን ልቀት ቅነሳ ያመጣው ውጤት ተመዝኖ አገሪቱ ክፍያ እንድታገኝ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል።
"የሬድ ፕላስ" የምዕራፍ አንድ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ ለማስቻል ላለፉት አምስት አመታት ሲተገበር ቆይቷል።