"የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ስም በመጠቀም አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ውድድሮች በኢትዮጵያ እንዲዘጋጁ መሥራት አለብን" - አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016(ኢዜአ)፦ "የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ስም በመጠቀም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች በኢትዮጵያ እንዲዘጋጁ መሥራት አለብን" ሲል የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሥራች አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ገለፀ።

አትሌቱ ይህን የገለፀው 23ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

23ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እሁድ ኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም ከ45 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በሚያደርጉት የሩጫ ውድድር ይከናወናል።

ከእነዚህም ውስጥ 15 አገራትን የሚወክሉ ከ200 በላይ ዓለም አቀፍ ተሳታፊዎችም እንደሚኖሩ ተገልጿል።

በለንደን የሚገኙ 200 ኢትዮጵያውያን ውድድሩ በሚደረግበት ቀንና ሰዓት ላይ በተመሳሳይ በቨርቹዋል ሩጫ ውድድር እንደሚሳተፉ አስታውቋል።

በየ500 ሜትሩም የሕክምና ባለሙያዎች ጣቢያ በማዘጋጀት ውድድሩ እንደሚከናወን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ገልጿል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሥራች አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ "የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ስም በመጠቀም አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ውድድሮች በኢትዮጵያ እንዲዘጋጁ መሥራት አለብን" ሲል ተናግሯል።

እንደ ኬንያና ዩጋንዳ ያሉ ሀገሮች የአፍሪካ ሻምፒዮና እና ዓለምአቀፍ ውድድሮችን ከዚህ ቀደም ማዘጋጀታቸውን ገልፆ፤ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ውድድር እንዳላት ውጤታማነት የማዘጋጀት ዕድል አላገኘችም ብሏል።

ስለዚህ በቀጣይ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አንድ ዓለም አቀፍ ውድድር በኢትዮጵያ እንዲዘጋጅ እንደሚሰራ ጠቁሟል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል።

ኢትዮጵያንም በዓለምአቀፍ መድረክ ገፅታዋን በበጎ ጎኑ በመገንባትና የስፖርት ዲፕሎማሲውንም በማጠናክር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የበኩሉን ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል ብለዋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ1993 ዓ.ም የተጀመረና በየዓመቱ የሚከናወን የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ነው።

በዘንድሮው ውድድር በሁለቱም ፆታዎች አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች 200 ሺህ ብር፣ ሁለተኛ ለሚወጡ 100 ሺህ ብር እና ሦስተኛ ለሚወጡት ደግሞ የ50 ሺህ ብር ሽልማት መዘጋጀቱ ተጠቅሷል።

ከ4ኛ እስከ 8ኛ ለሚወጡ አትሌቶችም ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን፤ በውድድሩ ሪከርድ ለሚያሻሽሉ አትሌቶች የ50 ሺህ ብር ተጨማሪ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ተገልጿል።

የዘንድሮውን ውድድር በክብር እንግድነት የሚያስጀምሩት በባርሴሎና ኦሊምፒክ አትሌት ደራርቱ ቱሉን በመከተል በ10 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ያመጣችው ደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት ኤላና ሜር እና ታዋቂው እንግሊዛዊ ኮሜንታተር/ተንታኝ/ ቲም ሃቺንግስ እንደሆኑ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም