ቀጥታ፡

የውጭ ቀጥተኛ  ኢንቨስትመንትን በስፋት ለመሳብ  ከክልሎች ጋር የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016 (ኢዜአ)፦  የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በስፋት ለመሳብ ከክልሎች ጋር  የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ገለጹ።

ኮሚሽኑ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ  በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።

በተለይም የሀገሪቱን ዕድገት ለማሳለጥ በክልሎች ከሚገኙ አስፈጻሚ አካላት ጋር በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትና እና ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የክልሎችን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም በመለየት የውጭ ባለሃብቶች ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑም ነው ብለዋል። 

ኮሚሽኑ በ2016 በጀት ዓመት ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ዕቅድ ይዞ ወደ ተግባር መግባቱን  ገልጸዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል  ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ።

አፈጻጸሙም ከሩብ ዓመቱ እቅድ 60 በመቶ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ የዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ኢንቨስትመንትን ወደ ሀገሪቱ የመሳብ ግብን በስፋት መያዙን ተናግረዋል።

በዚህም የሀገሪቱን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ምች ሁኔታዎች መፍጠር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አንስተዋል።

የህግ እና የመዋቅር ማሻሻያዎችን በማድረግ የተሻለ ምህዳር እንደሚፈጠር በመጠቆም።

የአዲስ አበባ ኢንቨትመንት ኮሚሽን የዕቅድና በጀት ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተር እናትነሽ ታመነ በበኩላቸው፤  በመዲናዋ ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ ቢሮው እየሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም ኢንቨስተሮች ባሉበት ቦታ ሆነው ምቹና ቀልጣፋ የፈቃድ አገልግሎት እንዲያገኙ የኦንላይን ስርዓት መዘርጋቱንና የተሻለ አፈጻጸም መኖሩንም ገልጸዋል።

በመዲናዋ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር ልዩ የማስተዋወቂያ ተግባራት እንደሚከናወኑ በመጠቆም።

የድሬዳዋ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የጥናትና ፕሮሞሽን ቡድን መሪ አበራ መንግስቱ በበኩላቸው፤ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች  ኢንቨስትመንታቸውን እንዲያስፋፉ ምቹ ሁኔታዎችን የማስተዋወቅ ስራ በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም