ኢትዮ-ቴሌኮም አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮ-ቴሌኮም የፋይናንስ አካታችነትንና አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማስፋት የሚያከናውናቸውን  ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገለፁ። 

ኢትዮ-ቴሌኮም የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለትን አስተዳደር ሥርዓት፣ የነዳጅ ኩፖንና የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ዲጂታል ለማድረግ የሚያስችል አሠራር ዛሬ ይፋ አድርጓል።  

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ነዳጅን የተመለከቱ የዲጂታል ሥርዓቶች የነዳጅ ኩባንያዎች የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ያስችላል።


 

ይህም ግልጽነት ለመፍጠርና ትክክለኛ መረጃዎች በወቅቱ ለማግኘት የሚያስችል ነው ተብሏል። 

ይህም ብቻ ሳይሆን የነዳጅ ማደያዎችን የአገልግሎት አማራጭ ለማሳደግ፣ ግብይቶችን ለማሳለጥ እንዲሁም የገንዘብ ፍሰትን ለማሻሻል ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ነው ያስረዱት።  

የሦስተኛ ወገን የመድን አገልግሎት በዲጂታል ለመስጠት የሚያስችለው ሥርዓትም በትክክለኛ መረጃ ላይ መሠረት ያደረገ የተማከለ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።  

 ኩባንያው የተለያዩ ዘመናዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ የአገሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ለማስቀጠል የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።  

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ በበኩላቸው፤ የዲጂታል አሠራሮቹ ዘመናዊ የነዳጅ ግብይት ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል። 


 

በተለይም የዲጂታል ኩፖን መረጃዎችን ለመቆጣጠር እንዲሁም ደኅንነቱ የተጠበቀ ግብይት ለማካሄድ ያስችላል ሲሉም ነው ዋና ዳይሬክተሯ የተናገሩት።  

የኢትዮጵያ መንገድ ደኅንነትና መድኅን ፈንድ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አባሶ፤ የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ዲጂታል መሆን በርካታ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።  

ይህም በኢንሹራንስ ሂደቶች ውስጥ የሚከሰቱትን ተግዳሮቶች ለመቀነስ ያግዛል ነው ያሉት።

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም