ቀጥታ፡

"የመደመር ጉዞ'' የፓናል ውይይት ነገ በድሬዳዋ ከተማ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያዘጋጀው ምዕራፍ ስድስት "የመደመር ጉዞ'' የፓናል ውይይት መድረክ ነገ በድሬዳዋ ከተማ ይካሄዳል።

መድረኩ ''መደመር ለቀጣናዊ ብልጽግና'' በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ሲሆን፣ የመደመር እሳቤ ለቀጣናዊ ትስስርና ብልጽግና ያለውን ሚና በተመለከተ  ውይይት ይደረግበታል።

የመደመር ጉዞ የወይይት መድረኮች ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገር በቀል እውቀቶችን መሰረት በማድረግ  “መደመር”፣ “የመደመር መንገድ” እና “የመደመር ትውልድ“ በሚሉ ርዕሶች ለንባብ ያበቋቸውን መጽሃፍት መሰረት ያደረጉ ናቸው።

በኢዜአ የሚዘጋጁት የመደመር ጉዞ መድረኮች የመደመር መጽሃፍቱ በያዟቸው እሳቤዎች ላይ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወያዩባቸው ናቸው። 

ኢዜአ ከዚህ ቀደም መሰል መድረኮችን በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ ጅግጅጋ፣ አሶሳ እና ሆሳዕና ያካሄደ ሲሆን፣ በድሬዳዋ ከተማ በነገው እለት የሚካሄደው መድረክ ምዕራፍ ስድስት መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም የተካሄዱ መድረኮችም በመደመር እሳቤ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገባቸውና የጋራ መግባባት የፈጠሩ ናቸው።

ነገ በድሬዳዋ ከተማ የሚካሄደው የምዕራፍ ስድስት ውይይት መድረክ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ ምሁራን በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቀጣናዊ ትስስርን እንዲያሳልጥ የተገነባው የድሬደዋ ነጻ የንግድ ቀጠና በጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ነሀሴ 8 ቀን 2014 ዓም ተመርቆ በይፋ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም