በአማራ ክልል 450 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብልን በቴክኖሎጂ ታግዞ ለመሰብሰብ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል 450 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብልን በቴክኖሎጂ ታግዞ ለመሰብሰብ ዝግጅት እየተደረገ ነው
ባህር ዳር፤ ህዳር 7/2016 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የተለያዩ የምርት መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከ450 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት የለማ ሰብልን ለመሰብሰብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አግደው ሞላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የደረሰን ሰብል በወቅቱ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ለመቀነስ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በክልሉ የሚገኙ 43 የሰብል መሰብሰቢያ ኮምባይነሮች የስንዴና ሌሎች ሰብሎችን የመሰብሰብ ስራ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም በ411 አነስተኛ የሰብል መውቂያ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ በቆሎ፣ ጤፍና ማሾ ሰብሎችን የምርት ብክነት ሊቀንስ በሚችል መልኩ እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙትን የሰብል ማጨጃና መውቂያ ኮምባይነሮች እንዲሁም አነስተኛ ማሽነሪዎችን የስራ ሰዓት በማራዘም የደረሱ ሰብሎችን ቅድሚያ ሰጥቶ ለመሰብሰብ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
የደረሰ ሰብል ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመታደግ እየተደረገ ባለው ጥረት በክልሉ በመኽር አዝመራ ከለማው 5 ሚሊዬን ሄክታር መሬት እስካሁን በ1 ነጥብ 8 ሚሊዬን ሄክታር ላይ የደረሰ ሰብል በሰው ኃይል መሰብሰብ እንደተቻለም አብራርተዋል።
በክልሉ አጠቃላይ በመኽር አዝመራው ከለማው መሬት 160 ሚሊዬን ኩንታል የተለያየ የሰብል ምርት እንደሚጠበቅም አስታውሰዋል።
በግማሽ ሄክታር መሬት ያለሙትን የስንዴ ሰብል ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ በኮምባይነር ለመሰብሰብ እንደተዘጋጁ የገለጹት ደግሞ የወንበርማ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ቸኮል ታደለ ናቸው።
እንዲሁም በግማሽ ሄክታር ያለሙትን የበቆሎ ሰብል በአነስተኛ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን በመታገዝ የምርት ብክነት ሊያስቀር በሚችል መልኩ ለመሰብሰብ አቅደው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ሰብልን በቴክኖሎጂ መሰብሰብ ሊደርስ የሚችለውን የምርት ብክነት ከማስቀረቱም በላይ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ሰብስቦ ለገበያ ለማቅረብ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው አስታውቀዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የደብረኤልያስ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አተረፍ አንዷለም እንዳሉት፤ በኩታ ገጠም በ2 ሄክታር መሬት ያለሙት የስንዴ ሰብል ለአጨዳ ደርሷል።
በቻሉት መጠን የሰው ጉልበት በመጠቀም የመሰብሰብ ስራውን እያከናወኑ ኮምባይነር ወደ አካባቢው እስከሚመጣ እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ባለፈው ዓመት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በ294 ሺህ 447 ሄክታር መሬት የለማ ሰብል መሰብሰብ ተችሎ እንደነበር ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።