በሦስት ወራት ከ76 ሺ በላይ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በሦስት ወራት ከ76 ሺ በላይ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት በተያዘው የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 76 ሺ 826 አዳዲስ ደንበኞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረጉን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር መላኩ ታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
ጎን ለጎንም የደንበኞችን እርካታ ለማረጋገጥ የሚረዱ የቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ሥራዎችን ጨምሮ በርካታ የውስጥ አሰራር ማሻሻያዎች በሥፋት እየተከናወኑ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት 600 ሺ ደንበኞች የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 76 ሺህ 826 አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በዚህም 11 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ያሉት።
በሩብ ዓመቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነቱን ለማረገጋጥ በተቋሙ በተሰሩ ሥራዎች 3 ሺ 825 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩንም አብራርተዋል።
ጎን ለጎንም በስምንት ከተሞች የኔትወርክ ማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ያልተቆራረጠ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
በቀጣይም የኤሌትሪክ ኃይል ያላገኙ የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮችን እንዲሁም ደንበኞችን ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ የኃይል መቆራረጥንና የኃይል ብክነትን ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።
ተቋሙ በሩብ ዓመቱ ከኃይል ሽያጭ ለመሰብሰብ ካቀደው 7 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር 6 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 83 በመቶ ማሳካት መቻሉን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 4 ነጥብ 4 ሚሊየን የሚጠጋ ደንበኞች አሉት።