ቀጥታ፡

ኪነ-ጥበብን ለሰላም ግንባታና የሕዝብን አብሮነት ለሚያጠናክሩ ጉዳዮች በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል አለብን - የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016(ኢዜአ)፦ኪነ-ጥበብን ለሰላም ግንባታና የሕዝብን አብሮነት ለሚያጠናክሩ ጉዳዮች በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል አለብን  ሲሉ ኢዜአ  ያነጋገራቸው የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡   

ሰላምና የአገር አንድነትን በማጠናከር ረገድ በሁለም የሥራ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች ኃላፊነት እንዳለባቸውም ነው የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ የተናገሩት፡፡ 

በተለይ ኪነ-ጥበብ ሕዝብን ለሰላምና ለአገር አንድነት በጋራ በማሰለፍ ረገድ ሚናዋ ጉልህ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ተዋናይ ካሌብ ዋለልኝ ኪነ-ጥበብና ሰላም የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን ይናገራል፡፡   

ከዚህ አኳያ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ሰላም አንድነትና ልማት እንዲመጣ ሕዝብን የማስተባበር ሚናችንን በአግባቡ መወጣት አለብን ነው ያለው፡፡

የአድዋ ድልን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያሳካናቸው ድሎች ሕዝብን ለማስተሳሰር ሚናቸው የጎላ መሆኑንም አብራርቷል፡፡

የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እነዚህ አቅሞችን በመጠቀም ረገድ በርካታ ሥራዎች እንደሚጠበቅባቸውም ነው የተናገረው፡፡

ከዚህ አኳያ ለሰላምና ለሕዝቦች አብሮነት መጠናከር ምን ያህል እየሰራን ነው ብለን መለስ ብለን ራሳችንን  መጠየቅ አለብን ብሏል፡፡         

የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ፍቅርና አንድነት ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ከኛ የሚጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው ብሏል።    

ለዚህ ደግሞ በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል ነው ያለው፡፡

 ተዋናይና ገጣሚ ዋሲሁን በላይ በበኩሉ አገር ለመገንባት ትውልዱ ላይ ጠንካራ የአገር ፍቅር ስሜት መፍጠር ወሳኝ መሆኑን አንስቷል።    

አሜሪካን የመሰሉ የበለጸጉ አገራት ትውልድ ላይ የሰሩት በኪነ-ጥበብ መሆኑን ጠቅሶ፤ እኛም በዚህ ረገድ ብዙ መሥራት አለብን ነው ያለው፡፡   

"በትብብር ሰላምን ማስፈን ፖለቲካ አይደለም" ያለው ተዋናይ ዋሲሁን፤ ከዚህ አኳያ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥቶ ተናግሯል፡፡   

ሰላምና አንድነትን በማስፈን ረገድ የመገናኛ ብዙኃን እና የኪነ-ጥበቡ ቤተሰብ በቅንጅት መሥራት እንዳለበትም ጥሪ አቅርቧል፡፡   

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም