የሕዝብ ቁጥር እድገትን ታሳቢ ያደረገ ኢኮኖሚ ለመገንባት የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ሁላችንም መስራት ይጠበቅብናል - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ቁጥር እድገትን ታሳቢ ያደረገ ኢኮኖሚ ለመገንባት የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ሁላችንም መስራት ይጠበቅብናል
ሐረር፣ ህዳር 7/ 2016 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የሚታየውን የሕዝብ ቁጥር እድገት ታሳቢ ያደረገ ኢኮኖሚ ለመገንባትና ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት የባህር በር ጥያቄ በሰጥቶ መቀበል መርህ ምላሽ እንዲያገኝ ሁላችንም መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ምሁራን ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤትነትን አስመልክታ እያራመደችው ያለውን አቋም የጎረቤት አገሮችም ሆኑ ሌሎች ዓለማት ጉዳዬ ብለው ሊወያዩበትና ሊያደምጡት እንደሚገባ አንስተዋል።
ጎረቤት አገሮችም ኢትዮጵያ እያነሳች ስላለው የወደብ ጉዳይ ጆሮ ሰጥተው በማድመጥ ራሳቸውን ለውይይት እንዲያዘጋጁ አፅንኦት መስጠታቸውም የሚታወስ ነው።
ኢዜአ ከሐረማያ፣ ከድሬዳዋና ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ጋር ባደረገው ቆይታም የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የሕዝብ ቁጥርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለሚገነባ ኢኮኖሚ ወሳኝ መሆኑን በማንሳት ጉዳዩ ምላሽ እንዲያገኝም የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህር አቶ ፍሬዘር ጥላሁን እንደሚሉት፤ የባህር በር ማግኘት ማለት የንግድ ሥራን ማሳለጥ ብቻ ሳይሆን የግብርና፣ የአሣ ሃብት ልማትና የቱሪዝም ሥራዎችን ለማቀላጠፍ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
"ኢትዮጵያ በ2030 የህዝብ ቁጥሯ እስከ 150 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል" ያሉት አቶ ፍሬዘር፣ በዚህም 60 በመቶው የሚሆነው ዕድሜው ከ24 ዓመት በታችና ለሥራ ዝግጁ ስለሚሆን የሥራ ዕድል ማመቻቸት ይገባል ብለዋል።
የንግድ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ፣ ኢኮኖሚውን የሚደግፉ ሌሎች መስኮችን ለማሳደግና ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የባህር በር ወሳኝ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ማብራሪያ ወቅታዊና ትክክለኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
ወደብ አልባ አገር መሆን የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴን እንዳይሳለጥ ከማድረግ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ እንዳለው የሚናገሩት አቶ ፍሬዘር "በአየር ትራንስፖርት አሊያም ወደብ በመከራየት የሚከናወን የንግድ እንቅስቃሴ አገሮችን ለከፍተኛ ወጪ ይዳርጋል፤ ኢኮኖሚያቸውንም በፈለጉት ልክ ለማሳደግ አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ህዝብ እና የኢኮኖሚ እድገቱን ከግምት በማስገባት “የባህር በር የህልውና ጉዳይ ነው” ያሉት አግባብ እንደሆነም አንስተዋል።
"የባህር በር ጉዳይ የማይሳካ ጉዳይ አድርጎ መውሰድ የለብንም" ያሉት አቶ ፍሬዘር፣ ለዚህም አይቻልም ሲባል የነበረውን ታላቁ የኢትዮዽያ ሕዳሴ ግድብን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮዽያ የቀጣናውን አሁናዊ ሁኔታ የምታውቅና የምትረዳ እንዲሁም "በሰጥቶ መቀበል እና በጋራ መልማት መርህ የምታምን በመሆኑ የባህር በር ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል ብቻ ሳይሆን ይገባታል" ሲሉም ገልጸዋል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር ናሊ ደበሊ በበኩላቸው ኢትዮዽያ የባህር በር የሌላት አገር መሆኗ የሚፈለገውን የኢኮኖሚው እድገት እንዳታስመዘግብ አንዱና ዋነኛ ምክንያት ነው።
በኢኮኖሚው የበለጸጉ አገራት አንዳንዶቹ ከሁለት በላይ የባህር በር ያላቸውና በወደቡም ኢኮኖሚያቸውን በማሳደግ ከፍተኛ ጥቅም እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ የባህር በር ማግኘቷ ኢንቨስትመንትን ጨምሮ የኢኮኖሚ እድገቱን ለማፋጠን ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የባህር በር ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መወያያ ማድረጋቸው ተገቢና የቀባይነት ያለው መሆኑንም አቶ ናሊ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የባህር በር የመጠቀም ፍላጎቷን አጀንዳ ማድረጓና ለዚህም ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች መጀመሯ ለነገ የተሻለች አገር ለመገንባት ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይ የባህር በር ጥያቄን የመጠቀም መብት ማንሳት እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ "ወቅታዊና ታሪካዊ ኃላፊነትን የመወጣት ጉዳይ ማየት ይገባል" ሲሉም አቶ ናሊ አውስተዋል።
ለዚህም ምሁራንና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ጉዳዩን ዓለምአቀፍ አጀንዳ በማድረግ የኢትዮጵያ የዓመታት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መረባረብ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።
አገራችን ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለማሳካት የጀመረችውን የባህር በር ጥያቄ ዕውን ለማድረግ መትጋቷ ዘላቂ የጋራ ዕድገትና መተማመንን ለማምጣት እንደሚያስችልም ምሁሩ ገልጸዋል።
"የባህር በርና አማራጭ የወደብ ጥያቄ ተገቢና ለኢትዮጵያ ህዝብ የህልውና ጉዳይ ነው" ያሉት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በድሩ ሂሪጎ ናቸው።
እሳቸው እንደሚሉት የኢትዮጵያ የግብርና፣ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች የልማት መስኮች ከውጪ በሚመጡ ቁሶች ላይ የተመሠረቱ በመሆኑ የባህር በር እና አማራጭ ወደብ ፍላጎቱ ተገቢ ነው።
አቶ በድሩ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥርና ኢኮኖሚው እያደገ በመምጣቱ ይህን የሚሸከም ኢኮኖሚ በቀጣይነት ለመገንባት የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ የባህር በር ማግኘት ያስፈልጋል።
ይህ ካልሆነ መጪው ትውልድ ችግር ውስጥ እንደሚወድቅ ያመለከቱት አቶ በድሩ፣ ኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ድርሻዎችን በማጋራት የባህር በርና አማራጭ ወደብ ለማግኘት ያሳየችው ፍላጎት ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።