ቀጥታ፡

የደቡብ ሱዳን ሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ኢትዮጵያ ገንቢ ሚና ትጫወታለች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/ 2016(ኢዜአ):-" የደቡብ ሱዳን ሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ኢትዮጵያ ገንቢ ሚና ትጫወታለች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

አቶ ደመቀ በተ.መ.ድ የደቡብ ሱዳን ልዩ ተወካይ እና የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ ሀላፊ ኒኮላስ ሮላንድ ሌይቦርን ሃይሶም ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

የደቡብ ሱዳን ፀጥታ እና ሰላም እንዲረጋገጥ እና የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ኢትዮጵያ ያላትን ሚና እየተወጣች መሆኑን ተናግረዋል።

በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የታሪክ የባህል እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መነሻ በማድረግ የቀጠናው ሰላም እንዲረጋገጥ እና ሰላም እንዲፀና እየሰራች መሆኑን ለልዩ ተወካዩ ኒኮላስ ሮላንድ ሌይቦርን ሃይሶም አስረድተዋል።

በደቡብ ሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ በአገሪቱ አንፃራዊ ሰላም በመስፈኑ ኢትዮጵያ ለሰላም የሚደረገውን ጥረት ትደግፋለች ብለዋል ።

በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በተቀናቃኞቹ መካከል መተማመን፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ ተቋማት፣ ጉረቤት አገራት እና ዓለምአቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባው አፅንኦት ሰጥተዋል ።

በጎረቤት አገራት በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች ሀገራት በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ወደ አገሪቱ እየገቡ ቢሆንም ከ 1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተሟላ አገልግሎት በመስጠት ኢትዮጵያ እያስተናገደች መሆኗን አስረድተዋል ።

በተ.መ.ድ የደቡብ ሱዳን ልዩ ተወካይ እና በተመድ የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ ሀላፊ ኒኮላስ ሮላንድ ሃይሶም ኢትዮጵያ የጉረቤት አገራት ሰላም እንዲረጋገጥ ያላት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ተመድ ለሚያደርገው የሰላም ስምምነት አፈፃፀም ኢትዮጵያ ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል።

በደቡብ ሱዳን በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ በአፍሪካ ኀብረት፣ ኢጋድ እና ተመድ በጋራ እንዲሰሩ የኢትዮጵያ ተሳትፎ ጉልህ በመሆኑ እገዛው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላም ማስከበር ተልኮ የምታደርገውን ድጋፍ ከተመድ ጋር በመሆን ያላትን አጋርነት እና አስተዋጽኦ ልዩ ተወካይ አድናቆት መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም