የኢትዮጵያን የባህር በር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መቃኘት ይገባል -አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የባህር በር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መቃኘት ይገባል -አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የባህር በርና የወደብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጉዳዩ ላይ ያሉ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መመልከት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ ገለጹ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያዘጋጀው የፍትሐዊ ወደብ አጠቃቀም ልዩ ሴሚናር "ፍትሐዊ የወደብ አጠቃቀም ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ተደራዳሪ ቡድን አባል አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ሕግ አኳያ ያለውን አንድምታ አስመልክቶ የመወያያ ጸሑፍ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር የመጠቀም ጥያቄና ፍላጎት የረጅም ጊዜ የታሪክ መሰረት እንዳለው አምባሳደር ኢብራሂም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፍላጎት የባህር በርና ወደቦችን በሰጥቶ መቀበልና የአገራትን ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ መጠቀም መሆኑን ገልጸዋል።
የአገሪቷ ፍላጎት ዓለም አቀፍ ሕግን መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው እ.አ.አ በ1982 የፀደቀውን ዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚ ለመሆን ከዚህ ቀደም የባህር በር የሌላቸው አገራት የባህር በር ካላቸው አገራት ጋር በመነጋገር ተጠቃሚነታቸውን ያረጋገጡባቸውን ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መመልከት አለባት ነው ያሉት አምባሳደሩ።
ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ሰፊ የዲፕሎማሲ ውይይቶችን ከአገራት ጋር ማድረግ እንደሚጠበቅባትም ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የባሕር በር የሌላቸው የአፍሪካ አገራት የሚያነሷቸውን የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የበኩሉን ሚና ሊጫወት እንደሚገባና ቀጣናዊ ተቋማት ለጉዳዩ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ውይይት የሚያስፈልገው መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያም እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጉዳዩ ላይ ውይይቶችን በማዘጋጀት ሳይንሳዊ ምክረ ሃሳቦችን ማፍለቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የቀጣናው አገራት ምሁራን ለመንግስታት ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች መሰረት የሚጥሉ ተከታታይ ምክክሮችን በማድረግ የመፍትሔ አማራጮችን እንዲያመላክቱም ጠይቀዋል።
በሴሚናሩ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፣የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች የዩኒቨርስቲ ምሁራንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።