መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅና የጋራ ትርክትን ለማስረፅ ትኩረት መስጠት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅና የጋራ ትርክትን ለማስረፅ ትኩረት መስጠት አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016(ኢዜአ)፦መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ክብርና ብሔራዊ ጥቅም ለሚያስከብሩ ና የጋራ ትርክትን ለሚያሰርፁ ይዘቶች ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ተገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባሳለፍነው ማክሰኞ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያ ዋነኛው ችግር አባባሽ ጉዳይ የተዛባ ትርክት ነው ብለዋል።
በመሆኑም በአሉታዊ ትርክት ልዩነትን ማስፋትና መዳከም እንጂ ትርፍ የማይገኝ በመሆኑ አብሮነትን በመቀበል ታላቅ ሀገራዊ ትርክት መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ ውስጥ የሀገርን ገመና አሳልፈው የሚሰጡ ዘገባዎችን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸውንም ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሃን የሀገርና የህዝብን ጥቅም የሚያስከብሩ ዘገባዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
ኢዜአ ይህን በተመለከተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠን አነጋግሯል።
የወል ትርክት አለመግባባቶችን ለማስወገድ፣ አሰባሳቢ የሆነ ማንነትን ለመፍጠር እንዲሁም ልዩነቶችን ለማስወገድ እንደሚጠቅም አንስተዋል።
ከዚህ አኳያ መገናኛ ብዙሃን በሕዝቦች መካከል የጋራ ትርክት ምህዳር እንዲፈጠር መስራት እንዳለባቸውም ነው የገለጹት፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ፤ አገር በሕዝቦች አንድነትና አብሮነት መሰረት ላይ እንድትጸና አሰባሳቢ የሆነ ትርክት አሰፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ መገናኛ ብዙሃን ጠንካራ ሀገር ለመፍጠርና አሳበሳቢ ትርክትን ለማህበረሰቡ ለማስረፅ ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩሉ፤ መገኛና ብዙሃን ለህብረተሰብ የአተሳሰብ ግንባታ መስራት እንደሚገባቸው ገልጿል።
መገናኛ ብዙሃን ሕዝቡ በአብሮነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚሻገርበትን መንገድ ማመላከት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ አገራዊ ምክክሩ እንዲሳካም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን የሚና መደበላለቅ ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ፤ ለዚህም የሚሰሩበትን ትክክልኛ አውድ ማወቅ አለባቸው ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት በአግባቡ አውቆ ለማስጠበቅ መስራት እንዲሁም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን በቅጡ የተረዳ አጀንዳን መቅረፅና ወደ ህዝቡ ማስተጋባት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
ጋዜጠኛ ጥበቡ በበኩሉ፤ መገናኛ ብዙሃን የልዩነት ገመናን ለሚሸፍኑ፣ የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ ሉዓላዊነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለሚያጎለብቱ ይዘቶች ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ተመዝግበው በስራ ላይ የሚንቀሳቀሱ ከ150 በላይ የህዝብ፣ የንግድ፣ የማህበረሰብ እና የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸው ተገልጿል።