ኢትዮ-ቴሌኮም የትራንስፖርት እና የነዳጅ አቅርቦትን የሚያዘምን ሥርዓት ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ-ቴሌኮም የትራንስፖርት እና የነዳጅ አቅርቦትን የሚያዘምን ሥርዓት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮ-ቴሌኮም የትራንስፖርት እና የነዳጅ አቅርቦትን የሚያዘምን የቴክኖሎጂ ስርዓት ይፋ አደረገ።
ዛሬ ይፋ የሆነው ስርዓት ዲጂታል የነዳጅ መሙያ ኩፖን፣ ዲጂታል የሶስተኛ ወገን መድህን እና ዲጂታል የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ያካተተ ሲሆን፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ይቀርፋል ተብሏል።
ለአብነትም የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለትን በተማከለ የዲጂታል ሥርዓት ለማሳለጥ እንደሚያስችል ተገልጿል።
በወረቀትና በሰው ንክኪ የሚፈጸም የነዳጅ ኩፖን ሽያጭ አገልግሎት አሰራርን በዲጂታል ኩፖን በመቀየር እመርታዊ ለውጥ እንደሚያመጣም ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል የሶስተኛ ወገን መድህን አገልግሎትን በዲጂታል ለመስጠት እንደሚያስችል ነው የተነገረው።
በመርኃ ግብሩ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ ደገፉ፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ፣ የመንገድ ደህንነት እና መድህን ፈንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አባስ እና የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ እስመለዓለም ምህረቱ ተገኝተዋል።