ቀጥታ፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የኩፍኝ በሽታን መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው

ሚዛን አማን ፤ ህዳር 07/2016 (ኢዜአ) ፦በክልሉ የኩፍኝ በሽታን ለመቆጣጠር ውጤታማና የተቀናጀ የመከላከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይሌ ዘውዴ ለኢዜአ እንዳሉት የበሽታው ስርጭት አሁን ከቀን ወደ ቀን እየቀነሰ መጥቷል።

በሽታው በስፋት የታየበት ምዕራብ ኦሞ ዞን ውስጥ ከፌዴራል ጀምሮ በተዋቀረ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ግብረ ኃይል በተደረገው ጥረት ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ከጥቂት ህሙማን በስተቀር የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያስችል ደረጃ ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

ለዚህም በሁሉም አካባቢዎች በርብርብ እየተሠራ ያለው የተቀናጀ የመከላከል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የቢሮ ሃላፊው አውስተዋል።

የምዕራብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሼማጂ ጉርጭማ ከነሐሴ አጋማሽ 2015 ዓ/ም ጀምሮ በዞኑ ባሉ ስምንት ቦታዎች የኩፍኝ በሽታ መከሰቱን አስታውሰው በተደረገው የተቀናጀ ርብርብም ጉዳት ለማድረስ በማይችልበት ሁኔታ ላይ እንዲገኝ ተደርጓል ብለዋል።

በሽታውን ለመቆጣጠር ከ20 የሚበልጡ ድንበር የለሽ ሀኪሞች በዞኑ ተንቀሳቅሰው እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የሚዛን አማን ከተማን ጨምሮ በሽታው በታየባቸው ወረዳዎች ክትባት እየተሰጠ እንደሚገኝና ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዞኑ የሚዛን ጤና ጣቢያ ዳይሬክተር ወይዘሮ እርጎዬ ገብሬ ያለፈውን ሳምንት ጨምሮ በዚህ ሳምንት ምንም አይነት የኩፍኝ ታማሚ በተቋሙ እንዳልተመዘገበ ተናግረዋል።

ወላጆች ልጆቻቸውን ከኩፍኝና መሰል በሽታዎች ለመከላከል በአቅራቢያቸው በሚገኝ የጤና ተቋም ቀርበው የማስከተብ ኃላፊነታቸውን ሳይዘናጉ እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በጤና ጣቢያው ልጆቻቸውን ሲያስከትቡ ያገኘናቸው ወይዘሮ ገነት ወልዴ የክትባት ጊዜን ጠብቀው ልጆቻቸውን እንዳስከተቡ ተናግረዋል።

ሌላዋ ልጃቸውን ያስከተቡ እናት ወ/ሮ ካሰች ማሞ በበኩላቸው በአካባቢው የተከሰተው የኩፍኝ በሽታ በልጆቻቸው ላይ ጉዳት ከማስከተሉ አስቀድሞ ማስከተባቸውን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም