ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ለመጠቀም በቀጣናው ያሉ የኃይል አሰላለፎችንና ተለዋዋጭ የሆኑ ሁኔታዎችን ያማከለ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን ይገባታል   

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የባህር በር ለመጠቀም በቀጣናው ያሉ የኃይል አሰላለፎችንና ተለዋዋጭ የሆኑ ሁኔታዎችን ያማከለ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን እንደሚገባት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ዶክተር በለጠ በላቸው ገለጹ።

ፍትሐዊ የወደብ አጠቃቀምን አስመልክቶ የተዘጋጀ ልዩ ሴሚናር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ዩኒቨርስቲው ያዘጋጀው ሴሚናር "ፍትሐዊ የወደብ አጠቃቀም ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ልማት" በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ዶክተር በለጠ በላቸው የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ከጂኦፓለቲካ አንጻር ያለውን አንድምታ አስመልክቶ የመነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከስትራቴጂካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ደህንነት መስኮች አኳያ ተገቢነት ያለው መሆኑን ዶክተር በለጠ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት፣ የኢኮኖሚ አቅምና የእድገት ፍላጎት አንጻር የባህር በር የሌላት አገር መሆኗ የሚያስቆጭ ነው ብለዋል።

የቀይ ባህር ውስብስብ የሆነ የኃያላን ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲ ፍላጎት ያለበት ቀጣና መሆኑን ጠቅሰው አገራቱ ጥቅማቸውን ለማሳካት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ለመጠቀም በቀጣናው ላይ ያሉ የኃይል አሰላለፎችንና ተለዋዋጭ የሆኑ ሁኔታዎችን ያማከለ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን እንደሚገባት ነው ዶክተር በለጠ ያስረዱት።


 

ለዚህም ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራትና ቀጣናው ላይ ፍላጎት ካላቸው አገራት ጋር ጥልቅ የሆነ የዲፕሎማሲ ውይይት ማድረግና ፍላጎቷን እውን የሚያደርጉ ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ስብስቦችን መቀላቀል እንዳለባት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በጥንቃቄና በበሳልነት መያዝ እንዳለበት አመልክተዋል።

በሴሚናሩ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፣የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች የዩኒቨርስቲ ምሁራንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ጉዳዩን የተመለከቱ ሌሎች ጽሑፎችም ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም