በህብረ ብሔራዊ አንድነት የፀና ኢትዮጵያዊነት የታላቁ ትርክት መሰረት መሆን እንዳለበት ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በህብረ ብሔራዊ አንድነት የፀና ኢትዮጵያዊነት የታላቁ ትርክት መሰረት መሆን እንዳለበት ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016 (ኢዜአ)፦በህብረ ብሔራዊ አንድነትና ለሀገር ክብር አብሮ በመሰዋት የጸናው ኢትዮጵያዊነት የታላቁ ትርክት መሰረት መሆን እንዳለበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የታሪክና የስነማህበረሰብ ምሁራን ገለጹ።
የተዛቡ ነጠላ ትርክቶች አንዳንድ ሀገራትን እስከማፍረስ መድረሳቸውንና ለኢትዮጵያም ፈተና መሆናቸውን ተናግረዋል።
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አየለ በከሬ፤ ትርክት በየትኛውም አካባቢ ያለን ማህበረ ፖለቲካዊ ስርዓት ለማንበርና ለመቅረፅ ጥቅም ላይ የሚውል ዘዴ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ትርክቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ጠቃሚና ጎጂውን መለየት እንደሚገባ አንስተዋል።
የአንድን ቡድን ማንነት፣ ሃይልና ምኞት በሌሎች ላይ ለመጫንና የበላይ ለማድረግ የሚሰነዘሩ ነጠላ ትርክቶች የግጭት አዙሪት ውስጥ የሚያስገቡና ሀገራዊ አንድነትን የሚያላሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከታሪክ የተወሰኑ መረጃዎችን አዛብቶ ለሚፈልጉት የርዕዮተ ዓለምና አፍራሽ ዓላማ ማስፈጸሚያ ማዋል በሩዋንዳ ካስከተለው እልቂት መማር እንደሚገባም አንስተዋል።
ላለፉት የተወሰኑ አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከታላቁ ትርክት ይልቅ የተዛቡ ነጠላ ትርክቶች ተንሰራፍተው መቆየታቸውንም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የሶሲዮሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘላለም ተፈራ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ትርክት ማህበረሰባዊ ባህልን እና መፃኢ ፍላጎትን ለማሳወቅ፣ ማንነትና ታሪክን ለማፅናት፣ ሀገርን ለመጠበቅ አርበኝነትን ለማምጣት፣ የሀገር ፍቅርን ለማላበስና አገርን በሁለንተናዊ መልኩ ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው።
ነጠላ ትርክቶች የአንድን ቡድን ገፅታ መገንባት ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸውን በማንሳት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ንዑሳን ትርክቶች የተገነቡበት መንገድ ሀገርን ለችግር የዳረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ታላቅ ሀገር እና ማህበረሰብ ለመገንባት የወል እውነቶች ላይ የተመሰረተ አሰባበሳቢ ትርክት መገንባት እንደሚገባም ምሁራኑ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ብዝሃ ማንነት ያላት ሀገር እንደመሆኗ መጠን ታሪኳ በአብሮነትና በቅራኔ የተሞላ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን አብሮ የመኖር ብቻ ሳይሆን ሀገረ ምንግስትን ለረጅም ዘመን በማፅናት፣ ለሀገር ዳር ድንበር መከበር አብሮ በመሰዋት ሞትን የተጋሩ አስደናቂ ህዝብ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል ምሁራኑ።
ኢትዮጵያ በረጅም የሀገረ መንግስት ታሪክ፣ ለዘመናት ተከብሮ በኖረ የሀገር ሉዓዊነትና ነጻነት እንዲሁም በገናና የጦርነት ድሎች የምትታወቅ መሆኗ ለትርክት ግንባታ ሚናው የላቀ እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህም ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያዊነት ላይ እንደማይደራደሩ ያሳየ ነው ያሉት ምሁራኑ፤ ገናናዋን ኢትዮጵያ ለመገንባትም በህብረ ብሔራዊ አንድነት የፀናው ኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሰረተ የወል ትርክት መገንባት ተገቢ ነው ብለዋል።
ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር፣ ብዝሃ ማንነት፣ የተፈጥሮ ሀብትና የታላቅነት ታሪክ መኖሩ፤ ለሁሉም ማህበረሰብ የምትመችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በመሆኑም የተዛቡ የልዩነትና የግጭት ቀስቃሽ ትርክቶችን ለማስቀረት መንግስት፣ ማህበረሰቡና ሚዲያው በትኩረት መስራት አለባቸው ነው ያሉት።
የነገዋን ኢትዮጵያ የመገንባት ሃላፊነት በትውልዱ ላይ መውደቁን ጠቅሰው፤ ለዚህ ስኬት አብሮነትንና ግብረ ገብነትን የሚያላብሱ ትርክቶች ላይ ማተኮር እንደሚገባም ጠቁመዋል።