ቀጥታ፡

የወንጀል ድርጊቶችን አስቀድሞ በመከላከል በዜጎችና ሀገር ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሁሉንም የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል-ፍትሕ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2016(ኢዜአ)፡- የወንጀል ድርጊቶችን አስቀድሞ በመከላከል በዜጎችና ሀገር ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሁሉንም የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።

የፍትሕ ሚኒስቴር አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ ሰነድ ላይ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።

አገር አቀፍ የተቀናጀ ወንጀል መከላከል ስትራቴጂ በሀገርና ህዝብ ሰላም፣ ደህንነትና ጥቅም ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በመከላከልና በመቀነስ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስጠበቅ በ2012 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀ ነው።

ስትራቴጂው የሽብር፣ በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ፣ ከባድ የኢኮኖሚና ከገንዘብ ጋር ተያይዘው የሚፈጸሙ፣ ግድያና ውንብድና፣ በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ፣ የሙስና፣ በሰው የመነገድና ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር፣ የመንገድ ትራፊክ ህግ ጥሰት እና በዜጎች ሰላምና ደህንነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በቅንጅት ለመከላከል የሚያስችል ነው።

እነዚህ ወንጀሎች ውስብስብና ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው ቀድሞ ለመከላከል ከተለያዩ ተቋማት በጋራ መስራት የሚያስችል የማስፈጸሚያ ሰነድም ተዘጋጅቷል።

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ወንጀል የዜጎችን መሰረታዊ ህይወት በማናጋት የሀገርን ህልውና የሚፈታተን ማህበራዊ ተግዳሮት ነው።

ወንጀልን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም አስቀድሞ በመከላከል የሚያደርሰውን ጉዳት መቀነስ እንደሚቻል ተናግረዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያ የወንጀል ድርጊቶችን ቀድሞ ለመከላከል በሚኒስትሮች ምክር ቤት አማካኝነት አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከያ ስትራቴጂ በ2012 ዓ.ም ማጽደቋን አስታውሰዋል።

ስትራቴጂው በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሳይሆን የቆየ መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን ላይ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ትብብር በመፍጠር ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የማስፈፀሚያ ሰነድ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ በበኩላቸው፤ ወንጀል ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ሳይለይ፤ ድንበር ሳይበግረው በማንናቸውም ጊዜና ቦታ የሚፈጸም ማህበራዊ ችግር መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ወንጀልን አስቀድሞ መከላከል እና ሲከሰት ደግሞ የጎላ ጉዳት ሳይደርስ ለማስወገድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ሁሉም ማህበረሰብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም