ቀጥታ፡

ወጣቶች የእግር ኳስ ጥበብን በትምህርት ቤቶች የሚቀስሙበት "ፉት ቦል ፎር እስኩል ፕሮጀክት" ይፋ ተደረገ

ድሬደዋ ፤ህዳር 6/2016 (ኢዜአ)፦ የዓለም እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ዋና ፀሐፊ ማዳም ፋጡማ ሳሞራ ተተኪ ወጣቶች የእግር ኳስ ጥበብን በትምህርት ቤቶች የሚቀስሙበትን "ፉት ቦል ፎር እስኩል ፕሮጀክት" በድሬደዋ ይፋ አደረጉ።

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ዘርፍ ያላትን ደረጃ ለማሳደግና ተተኪ ወጣቶች በእግር ኳስ ጥበብ መሠረታዊ ዕውቀት እንዲጨብጡ ያግዛል ተብሏል። 

በማዳም ፋጡማ ሳሞራ የተመራ የፊፋ ከፍተኛ ባለስልጣናትና አሰልጣኞች ልዑክ በድሬደዋ እየተሰሩ ያሉ የእግር ኳስ መሠረተ ልማት ግንባታዎችን ተመልክቷል።

በጉብኝቱ ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና የካቢኔ አባላት እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ተሳትፈዋል።


 

በፊፋ ዋና ፀሐፊ የተመራው ልዑክ በ50 ሚሊዮን ብር ወጪ በድሬደዋ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ የተነጠፈውን ሰው ሰራሽ የሣር ሜዳ እና ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባውን ሁሉን አቀፍ የስፖርት አካዳሚ ተመልክተዋል።

በዚሁ ጊዜ የፊፋ ዋና ፀሐፊ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በዓለም የእግር ኳስ ዘርፍ የሚገባትን ስፍራ እንድታገኝ እየተገነቡ ያሉ የስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አጋዥ ናቸው። 

እነዚህን ልማቶች በሚፈለገው ጥራት ተገንብተው ውጤት እንዲያመጡ ፊፋ የሚያደርገውን ሙያዊና ቴክኒካል ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

"ዛሬ በኢትዮጵያ የተገኘነው በፊፋ የተነደፈውን የትምህርት ቤቶች የእግር ኳስ ስልጠና ለማስጀመር" ነው ያሉት ዋና ፀሐፊዋ፣ ስልጠናው በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ተተኪ ወጣቶች በእግር ኳስ ቴክኒክና ታክቲክ እንዲሁም የዘርፉን ፕሮፌሽናል ጥበብ እንዲቀስሙ የሚያስችል ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ የካፍ መስራችና ታላቅ አገር መሆኗን ያስታወሱት ማዳም ፋጡማ፣ አሁን በድሬደዋና በመላው አገሪቱ እየተገነቡ የሚገኙ የእግር ኳስ መሠረተ ልማቶችን በማጠናከር በ2026 አፍሪካን በዓለም ዋንጫ ከሚወክሉ ዘጠኝ ወይም አስር አገሮች አንዷ ማድረግ እንደሚቻል ምኞታቸውን ገልፀዋል።

"በድሬዳዋ አስተዳደር እና በስፖርት ቤተሰብ የተደረገልኝ አቀባበልና መስተንግዶ የፊፋ ፕሬዚዳንት የሆንኩ ያህል ደስታና ኩራት እንዲሰማኝ አድርጎኛል" ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው እንዳሉት፣ የፊፋ ዋና ፀሐፊ ማዳም ፋጡማ ሳሞራ ለሁለተኛ ጊዜ ድሬደዋ በመምጣት ያደረጉት የሥራ ጉብኝትና የሰጡት ማበረታቻ ይበልጥ ለመስራትና የእግር ኳስ ደረጃና ከፍታን ለማረጋገጥ የሚያተጋ ነው።

ድሬደዋ ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ፈርጥ ሆነው የሚጠቀሱ ድንቅ ተጫዋቾችና በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ተሳታፊ የነበሩ ክለቦች ያፈራች ከተማ መሆኗን አስታውሰው፣ ይህንን ከፍታ ለመመለስ የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ በድሬደዋ ይፋ የተደረገው "ፊፋ ፉትቦል ፎር ስኩል ፕሮጀከት" ድሬዳዋ በዘርፉ ያላትን የቀድሞ ስም ለመመለስ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።

በመሆኑም ዛሬ ፊፋ ፉትቦል ፎር እስኩልስ በሚል ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት የድሬዳዋን የእግር ኳስ ከፍታ ዳግም የሚመልሱ ተጫዋቾችን ለማፍራት እንደሚያግዝ እንጠብቃለን ብለዋል።

ፊፋ ያስጀመረው "እግር ኳስ በትምህርት ቤት ፕሮጀክት" የእግር ኳስ ጥበበኞች መፍለቂያ ትክክለኛ ቦታውን እንዲያገኝ አስችሏል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ናቸው።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ፕሮጀክቱ ዕውን ለማድረግ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመፈራረም ስልጠናው በ60 ትምህርት ቤቶች የሚሰጥ ይሆናል። 

ከነዚህ ትምህርት ቤቶች መካከል የድሬዳዋ መልካጀብዱ ትምህርት ቤት አንዱ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ፊፋ ለስልጠናው 124ሺህ ኳሶችን መለገሱን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፣ ስልጠናው ለብሔራዊ ቡድን ምርጥና ተተኪ ተጫዋቾች ለማፍራት ብቻ ሳይሆን በእግር ኳስ ሂደት የመፍትሔ አካል የሚሆኑና መልካም ስነምግባር ያላቸው ዜጎችን ለማፍራት ያስችላል ብለዋል።

ስልጠናው የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ፌደሬሽኑ ከድሬደዋ አስተዳደር ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሰራም ነው አቶ ኢሳያስ የገለፁት።

በስነስርዓቱ ላይ የፊፋ ልዑካን ለአስተዳደሩ አመራሮች የተለያዩ ስጦታዎች ያበረከቱ ሲሆን የድሬዳዋ አስተዳደርም ለፊፋ ልዑክ የድሬዳዋ መገለጫ የሆኑ ማስታወሻዎች ሰጥቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም