ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው በጀት አመት ከካርጎ የጭነት አገልግሎት 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2016(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2015 በጀት ዓመት በካርጎ የጭነት አገልግሎት 750 ሺህ ቶን በማጓጓዝ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

አየር መንገዱ የካርጎ የደንበኞች ቀንን በማስመልከት በአዲስ አበባ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ ይገኛል።

በመረሃ-ግብሩ ላይ የትራንስፓርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዳንጌ ቦሩ፣ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ ዓለም አቀፍ የካርጎ ደንበኞችና ሌሎችም እንግዶች ታድመዋል።

በመድረኩም በካርጎ ጭነት ከፍተኛ አገልግሎት ተጠቃሚ ለሆኑ አስመጪና ላኪ ደንበኞች የእውቅና ሽልማት ተበርክቷል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አየር መንገዱ በካርጎ አገልግሎት ዘርፍ የላቀ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

አየር መንገዱ ባሉት 67 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች በ2015 በጀት አመት 750 ሺህ ቶን ጭነት ማጓጓዙን ገልፀዋል::

የካርጎ አገልግሎቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርም በመጪው ታህሳስ ወር በኤሌክትሮኒክስ የግብይት ሥርዓት ለሚገዙ እቃዎች የሚውል የካርጎ ማዕከል ወደ ሥራ ያስገባል ብለዋል።

በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥርዓቱ የሚገዙ እቃዎችን ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት በአዲስ አበባ በኩል ለማጓጓዝና የገበያ ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።

አየር መንገዱ ከአጠቃላይ ገቢው ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሰበሰበው ከካርጎ አገልግሎት መሆኑን ጠቅሰው የባለፈው በጀት ዓመት ካስገባው አጠቃላይ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር 2 ቢሊየን ዶላሩ ከካርጎና ሎጂስቲክ አገልግሎት የተሰበሰበ መሆኑ ተገልጿል።

አየር መንገዱ የ2023 ምርጥ የካርጎና ሎጂስቲክስ ኦፕሬተርና የአፍሪካ ምርጡ የካርጎ ኦፕሬተር በሚል በሁለት ዘርፎች ለአምስተኛ ጊዜ ተሸላሚ መሆኑ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም