ቀጥታ፡

በሰሜን ሲዳማ ዞን ለሕዳሴው ግድብ ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

ሐዋሳ፣ ህዳር 6/2016 (ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል ሰሜን ሲዳማ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ድጋፉ የተሰበሰበው የሕዳሴ ዋንጫ በዞኑ በቆየባቸው ሦስት ቀናት በተደካሄደ የገቢ ማሳባሰቢያ መርሃ ግብር ነው።

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የሰሜን ሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዲሱ ቃሚሶ እንደገለጹት፣ ለዓባይ ግድበ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ መላው ኢትዮጵያን አሻራቸውን በተለያየ መንገድ እያሳረፉ ነው።

የሲዳማ ህዝብም ለግድቡ ግንባታ በተለያየ መንገድ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተከናወኑ ሥራዎችና መንግስት የመሪነት ሚናውን በአግባቡ በመወጣቱ በአሁኑ ወቅት የግድቡ ፕሮጀክት አፈጻጻም የተሻለ ደረጃ ላይ መድረሱንም ጠቁመዋል።

"ግድቡ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት በማጠናከር ኢትዮጵያዊያንን ያስተሳሰረ በመሆኑ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ የህዝቡ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት የሕዳሴ ግድቡን ዋንጫ ከሃዋሳ ከተማ አስተዳደር መጥቶ በዞኑ በነበረው የሦስት ቀናት ቆይታ ህዝቡ በቦንድ ግዥና በአይነት ድጋፍ አድርጓል።

በዚህም በገንዘብ ከ26 ሚሊዮን 400ሺህ ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን፣ በአይነትም 24 ሰንጋዎች፣ በጎች፣ ፍየሎችና ዶሮዎች ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል።

ከተሰበሰበው ገቢ ከዕቅዱ 26 ከመቶ ብልጫ እንዳለው የተናገሩት አስተዳዳሪው፣ በድጋፉ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችንም አመስግነዋል።


 

የሲዳማ ክልል የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና ህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ክፍሌ ሃሜሶ በበኩላቸው፣ የሕዳሴው ግድብ የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ትልቅ አገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

የሲዳማ ህዝብም ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር ለግድቡ ግንባታ በተለያየ መንገድ ድጋፍ በማድረግ አሻራውን ሲያሳርፍ መቆየቱንም ገልጸዋል።

የሕዳሴ ዋንጫ ወደ ክልሉ መግባቱን ተከትሎ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች እያደረጉ ያሉት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አመልክተዋል።

"ዋንጫው በሃዋሳና በሰሜን ሲዳማ ዞን በነበረው ቆይታ ከዕቅድ በላይ ድጋፍ መሰብሰቡ ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነትና የአመራሩን የመሪነት ሚና ያሳያል" ሲሉም ገልጸዋል።

በቀጣይ ዋንጫው በሚዘዋወርባቸው ወረዳዎችና ዞኖችም ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንበታ ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል፡፡

በመርሃግብሩ የማጠቃለያ መድረክ ላይ ከተገኙት መካከል ከለኩ ከተማ አስተዳደር የመጡት አቶ ጌቱ ያአሞ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ዋንጫው ወደ ዞናቸው መምጣቱን ተከተትሎ በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብርም በራሳቸውና በልጆቻቸው ስም የ20 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡

ግድቡ ለትውልድ የሚሆን ሃብት በመሆኑ በልጆቻቸው ስም ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን ማሳረፋቸውንም ገልጸዋል።

"የሕዳሴው ግድብ የሁላችንም ሃብት በመሆኑ ድጋፋችንን ስናደርግ በደስታ ነው" ያሉት ደግሞ ከዞኑ ብላቴ ዙሪያ ወረዳ የመጡት አቶ ስዩም ቀማቸው ናቸው። 

ለግድቡ ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር ህዝቡን የማስተባባር ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዞኑ በተካሄደ የገቢ ማሳባሰቢያ ላይ የ30 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት የዜግነት ግዴታቸውን እንደተወጡም ገልጸዋል።

የሕዳሴው ዋንጫ ሰሜን ሲዳማ ዞን ቆይታውን አጠናቆ ወደ ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን የተሸጋገረ ሲሆን እስከ መጪው ህዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሲዳማ ክልል ቆይታውን ያጠናቅቃል ተብሎም ይጠበቃል። 

 

    

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም