ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ የልማት ዘርፎች እንዲሳተፉ መንግስት በፖሊሲ የተደገፉ አሰራሮችን ተግባራዊ አድርጓል - አምባሳደር ሙክታር ከድር - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ የልማት ዘርፎች እንዲሳተፉ መንግስት በፖሊሲ የተደገፉ አሰራሮችን ተግባራዊ አድርጓል - አምባሳደር ሙክታር ከድር
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2016(ኢዜአ)፦ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ የልማት ዘርፎች እንዲሳተፉ መንግስት በፖሊሲ የተደገፉ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረጉን አምባሳደር ዶክተር ሙክታር ከድር ተናገሩ።
በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ሙክታር ከድር የተመራ የልዑካን ቡድን በኢስተርንኬፕ ፕሮቪንስ፤ኢስትለንደን፣ኪንግዊልያምታዋን እና አካባቢው ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ጋር በዜጎች መብትና ደህንነት ማስጠበቅ፣ በዳያስፖራ ልማትና ተሳትፎ እንዲሁም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
ኤምባሲው በዜጎች መብትና ጥቅም ማስጠበቅ፣ በዳያስፖራ ልማትና ተሳትፎ ዙሪያ እያከናወናቸው ስላሉ ስራዎች እንዲሁም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በልዑኩ ገለጻ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
መንግስት በውጭ ለሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በሀገር ቤት በተለያዩ የልማት ዘርፎች እንዲሳተፉ በፖሊሲ የተደገፈ አሰራሮችን ዘርግቶ እያበረታታና እያስፈጸመ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ዳያስፖራው ዕድሎቹን በመጠቀምና ተሳትፎአቸውን በማጠናከር ራሳቸውንና ሀገራቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል፡፡
በአካባቢው የሚገኙ ዜጎች ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር እያጋጠማቸው ያሉትን የጋራ ችግሮችን ለመቅረፍ ከኤምባሲው ፣ ከአካባቢው ማህበረሰብና የአስተዳደር አካላት ጋር በመቀናጀት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተገልጿል።
በተለያዩ የወንጀል እንቅስቃሴዎች ውስጥ እየተሳተፉና በዜጎች ላይ የሥራና ደህንነት ሥጋቶችንና ችግሮችን እየፈጠሩ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥብቅ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ተላልፏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በተደራጁ ህገወጥ ቡድኖች አማካኝነት በኢትዮጵያውያን የንግድ መደብሮች ላይ የሚፈጸሙ ህገወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ከየአካበቢው የአስተዳደር አካላትና አመራሮች ጋር ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል፡፡
በአካባቢው የሚገኙ ዜጎች የማህበረሰብ አደረጃጀቶቻቸውን በማጠናከር ከኤምባሲውና ከአካባቢው የአስተዳደር አካላት ጋር ያሏቸውን ጠንካራና ተምሳሌታዊ የትብብር እንቅስቃሴዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል መግባባት ላይ መደረሱንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡